
ኢትዮ ሞኒተር፡ 07/01/2018፡- የተመድ መርማሪዎች የደቡብ ሱዳን ዜጎች በተራቡበት ሁኔታ ውስጥ ባለስልጣናቱ ረብጣ ቢሊየኖችን በሚያወጡ የሙስና ወንጀሎች መዘፈቃቸውን አጋልጠዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን “ደቡብ ሱዳን የግል ጥቅም ለማግኘት የሃገር ሃብትን በተቋማዊና ስርዓት መልኩ በሚሰርቁ በሊታ መሪዎች ተይዛለች” ብሏል።
የደቡብ ሱዳን አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2011 ነፃ ከወጣችበት አንፃር አሁን ላይ የሱን 1/4ኛ ሲሆን 2/3ኛ የሚሆነው ህዝቧም በረሃብ ይማቅቃል።
በምርመራው ከ2021-2024 የተደረገ ያልተገባ ክፍያ ሲጋለጥ በዚህ ዓመት የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙት ቦል ሜል ጋር ዝምድና ላላቸው የመንገድ ገንቢዎች ላልተሰራ መንገድ 1.7 ቢሊየን ዶላር ተከፍሏል ተብሏል።
አሜሪካ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቦል ሜልና ሁለት ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ ጥላ የነበረ ሲሆን በቅርቡ በነበሩ ውይይቶችም ይኸው ማዕቀብ እንዲነሳ የትራምፕ አስተዳደርን ጠይቀዋል ተብሏል።
ከ2021-2024 ባለው ጊዜ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከቦል ሜል ጋር ግንኙነት አላቸው ለተባሉ ድርጅቶች ከ2.2 ቢሊየን ዶላር በላይ ክፍያንም ፈፅሟል ተብሏል።
“ነዳጅ ለመንገድ” ተብሎ ለተሰየመውና ከነዳጅ የሚገኘውን ገንዘብ ለመንገድ ግንባታ ለማዋል ለታሰበው ለዚህ ፕሮጀክትም በአንድ ወቅት ከመንግስት አጠቃላይ ክፍያዎች 60 በመቶው ይወጣ እንደነበር በሪፖርቱ ተገልጿል።
እነዚህ የቦል ሜል ድርጅቶች ከ500 ሚሊየን ዶላር ያልበለጡ መንገዶችን ሲሰሩ የመንገዱን እርዝማኔ በመጨመር ኮንትራቶችን ጨምረው ከፍተኛ ገንዘብ ያስከፍላሉ።
ደቡብ ሱዳን ከነፃነቷ ወዲህ ከነዳጅ ሽያጭ ካገኘችው 23 ቢሊየን ዶላር ለህብረተሰቡ በሚጠቅም መልኩ የዋለው ጥቂቱ ሲሆን ለማሳያነት በ2022/23 የበጀት ዓመት ለመላው ሃገሪቱ የጤና ስርዓት ከተያዘው በጀት በላይ ለፕሬዚዳንቱ የጤና ክፍል ብቻ የተያዘው ይበልጣል።
የደቡብ ሱዳን የፍትህ ሚኒስቴር ለተመድ በፃፉት ምላሽ የተጠቀሰው መንግስት ካለው መረጃ ጋር አይገናኝም እንደዚሁም ካለው የኢኮኖሚ ችግር እና የነዳጅ ሽያጭ መቀነስ ጋር አይገናኝም በማለት ሪፖርቱን አጣጥለዋል።
ሙስና ደቡብ ሱዳናውያንን እየገደለ ነው ያለው ሪፖርቱ እነዚህ ከ2021-2024 የተፈፀሙ ክፍያዎች ጥቂቱ ብቻ ናቸው ብሏል።
ከ79 አካባቢዎች 76ቱ በከባድ ረሃብ ባለበት ሁኔታ ጥቂት ገንዘብ ብቻ ይህንን ለመቅረፍ መዋሉን ያሳየው ሪፖርቱ ሙስና በደቡብ ሱዳን ተቋማዊ ሆኗል ብሏል።