የሚኒሶታዋ የኮንግረስ አባል ኢልሃን ኦማር፣ ማክሰኞ ዕለት በሚኒያፖሊስ በተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ለደረሰባቸው ጥቃት፣ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የጥላቻ ንግግር” አስተዋጽኦ እንዳለው ገለጹ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 21/05/2018፡- ኢልሃን ትላንት ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ “ወደ ምርጫ ከተቀላቀልኩ ጀምሮ እውነታው የሚያሳየው፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በእኔና በምወክለው ማህበረሰብ ላይ የጥላቻ ንግግር በተጠቀሙ ቁጥር፣ የሚደርስብኝ የሞት ዛቻ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ነው” ብለዋል።
ማክሰኞ ምሽት በተደረገው ስብሰባ ላይ፣ ጄምስ ካዝሚርክዛክ የተባለ የ55 ዓመት ግለሰብ ወደ ኢልሃን በመጠጋት በሲሪንጅ የያዘውን ፈሳሽ ሊረጭባቸው ሲሞክር በቁጥጥር ስር ውሏል።
የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፈሳሹ “የአፕል ኮምጣጤ” ነበር። ጉዳዩን የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (FBI) በመመርመር ላይ ይገኛል።
የተጠርጣሪው የማህበራዊ ሚዲያ ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ግለሰቡ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊ እና ዴሞክራቶችን አጥብቆ የሚቃወም ነው።
ኢልሃን እንደገለጹት፣ ግለሰቡ ጥቃት ሊፈጽም የሞከረው “ትራምፕ ሶማሊያውያንን ለማፈናቀል የሰጡት ትዕዛዝ በቂ ውጤት አላመጣም” በሚል ተበሳጭቶና ኢልሃንን እንደ ሶማሊያውያን ጠባቂ አድርጎ በመቁጠሩ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ፣ ኢልሃን ኦማር ድርጊቱን ሆን ብላ አቀነባብራው ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ይታወሳል፡፡
“እሷን እንደማውቃት አጭበርባሪ ናት፣ እራሷን በራሷ ሳታስረጭ አልቀረችም” ሲሉ ለኤቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።



