የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የግብጹን ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲን ማገናኘት እንደሚፈልጉ ተናገሩ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/05/2018፡- ትራምፕ ሁለቱን መሪዎች ማገናኘት የሚፈልጉት፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ የሚፈታ ስምምነት ለማበጀት እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት፤ በስዊትዘርላንድ ዳቮስ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከግብጹ አቻቸው ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ነው።
ትናንት ረቡዕ በተካሄደው በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ውይይት ላይ፤ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የግብጽ አቻቸው ባድር አብደላቲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በንግግራቸው “በኢትዮጵያ ጠንካራ መሪ እንዳለ ሰምቼያለሁ። ይሁንና አንተን እንደማውቀው እሱን አላውቀውም። ነገር ግን ጠንካራ ሰው ነው። ሁለታችሁን ለማገናኘት እሞክራለሁ ” ሲሉ ተደምጧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የታላቁ ህዳሴን ግድብ ከዓለም ግዙፍ ግድቦች አንዱ እንደሆነ ጠቅሶ ” የግንባታውን ወጪ የሸፈነው እኛ ነን ” በማለት በድጋሚ ተናግሯል።
ትራምፕ ይህን ሲሉ የመጀመሪያ አይደለም፤ ከቀናት በፊት አንደኛ የስልጣን ዓመታቸው ሲያከብሩም ” እኛ ነን ፋይናንስ ያደረግነው ” ብለው ነበር። ከወራት በፊትም እንዲሁ ሲናገሩ ነበር።
ይሁን እንጂ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ መንግስት እና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትብብር እንደተገነባ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢትዮጵያንና ግብፅን ለማወያየት እንደሚፈልጉ ባለፈው ሳምንት ለፕሬዝዳንት አልሲሲ ብቻ ደብዳቤ የላኩ ሲሆኑ በአሁን ውይይታቸውም ለግብፅ የሚያዳሉ ሐሳቦች ሲያነሱ ተስተውለዋል።
ግብፅ ከሶስትዮሽ ቴክኒካል ኮሚቴ ውይይት ራሷ በማግለል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ ሌሎች ዲፕሎማሲዊ ጥረቶች ብታደርግም ኢትዮጵያ ግን ጫናዎቹ ተቋቁማ የህዳሴ ግድብን ማስመረቋ ይታወሳል።



