
ኢትዮ ሞኒተር፡ 28/12/2017፡- ቻይና 80ኛ የድል በዓልዋ በደማቅ ሁኔታ አክብራለች።
“ሺ ጂንፒንግ ከፑቲን እና ከኪም ጋር በአሜሪካ ላይ እያሴሩ ነው” ሲሉ ትራምፕ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ “ቻይና በማንኛውም ጉልበተኛ አትሸበርም” ብለዋል።
ቻይና 80ኛ ዓመት የድል በዓሏን ታይቶ በማይታወቅ ወታደራዊ ትርኢት አከበረች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ከሩሲያ እና ከሰሜን ኮሪያ መሪዎች ጋር በአሜሪካ ላይ ሴራ እያሴሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ትራምፕ ይህን ያሉት ቻይና 80ኛ ዓመት የድል በዓሏን የዓለም መሪዎችን በተገኙበት በግዙፉ ቲያናንመን አደባባይ በተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶች ቤከበረችበት ወቅተ ነው፡፡
በዚህም ወታደራዊ ትርኢት ላይ የቻይና ጦር አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህ ትርኢት ላይም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግን፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ የ26 ሀገራት መሪዎች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ታድመዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “እባካችሁ ለቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን በአሜሪካ ላይ ሲያሴሩ ሞቅ ያለ ሰላምታዬን ስጡልኝ” ሲሉ ጽፈዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ‘በቻይና፣ ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአሜሪካ ፈተና ነው’ የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በጽሁፋቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ ለቻይና የሰጠችውን ከፍተኛ ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፤ “በርካታ አሜሪካውያን ለቻይናውያን ድል ሕይወታቸውን ገብረዋል” ብለዋል፡፡
አክለውም “ብዙ አሜሪካውያን ለቻይና ድል እና ክብር ሲሉ ሞተዋል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በጀግንነታቸው እና በመስዋዕትነታቸው በትክክል እንደሚከበሩ እና እንደሚታወሱ ተስፋ አደርጋለሁ!” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ጃፓን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት እጅ የሰጠችበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት በሚከበረው የድል በዓል ላይ፤ “ቤይጂንግ፣ ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ በዋሽንግተን ላይ እያሴሩ ይገኛል” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
የትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ የዓለምን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስርዓት ካናጋ በኋላ፤ ቻይና ራሷን ከአሜሪካ ጋር ልታወዳደር እንደምትችል አስታውቃለች።
ቤጂንግ እና አጋሮቿ አሜሪካን ለመቃወም ዓለም አቀፍ ጥምረት ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ ትራምፕ በሰጡት ምላሽ፤ “አይሆንም በፍፁም ቻይና ትፈልገናለች” ብለዋል።
አክለውም “እኔ እንደምታውቁት ከፕሬዝዳንት ሺ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ቻይና ግን እኛ ከምንፈልጋት በላይ እሷ በጣም ትፈልጋለች:: በፍፁም አይታየኝም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ “በዓለም ላይ እጅግ ሀይለኛ ወታደር” እንዳላት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ “ወታደራዊ ሀይላቸውን በኛ ላይ ፈጽሞ አይጠቀሙበትም” ብለዋል፡፡
ቻይና ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት ላይ ዓለም አይቷቸው የማያውቃቸውን እጅግ የተራቀቁ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለዕይታ ያቀረበች ሲሆን፤ ከወታደራዊው ትርዒት በፊት 80ኛ ዓመት የድል በዓሉን በማስመልከት 80 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።
በዚህም ወታደራዊ ትርኢት ላይ ከቻይና ጦር ሠራዊት፣ ከባህር ኃይል እና አየር ኃይል የተውጣጡ ከ10 ሺሕ በላይ ወታደሮች ከቲያንመን አደባባይ ተሰልፈው ታይተዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ብዙ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን፤ በርካቶቹ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) የተገጠመላቸው ናቸው ተብሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የዓይን ብሌቶችን በብዛት የያዘውና እስከ 20 ሜትር ርዝመት ያለው AJX-002 ግዙፉ የባህር ሰርጓጅ አልባ ድሮን አንዱ ነው።
በተጨማሪም ቻይና መላውን ዓለም መሸፈን የሚችል የDF-5C አህጉር አቋራጭ ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ሚሳይል በወታደራዊ ሰልፉ ላይ አሳይታለች።
እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በመሬት፣ በባህር እና በአየር ላይ የተመሰረቱ ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ኃይሎቿን በወታደራዊ ሰልፍ ላይ ያሳየች ሲሆን፤ የሌዘር (ጨረር) የአየር መቃዎሚያዎች፣ የኑክሌር ማሳሪያዎች፣ ባለስቲክ ሚሳኤሎች እንዲሁም የተለያዩ ግዙፍ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለእይታ ቀርበዋል፡፡