አሜሪካ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ቤት አልባ ሰዎች ከተማዋን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ አዘዙ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/12/2017፡ ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ማህበራዊ ገፃቸው ባጋሩት ጽሁፍ በዋና ከተማዋ የሚኖሩ ቤት የሌላቸው ሰዎች በአፋጣኝ እንዲወጡ ወይም እንዲባረሩ ነው ያሳሰቡት።
ትራምፕ “ቤት የሌላቸው ሰዎች የሚቆዩምባቸው ቦታዎችን እንሰጣቸዋለን ፣ ነገር ግን ከዋሽንግተን ራቅ ባለ አከባቢ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ ወንጀለኞችን ለማሰር የፌደራል መኮንኖችን ለመጠቀም ቃል የገቡ ሲሆን ይህም “የጥቃት ወንጀልን ለማስቆም” ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
ትራምፕ በጥር ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በዋሽንግተን ዲሲ የነበረው የጥቃት ወንጀል መጠን በ30 ዓመታት ውስጥ ዝቅ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ ።
ትራምፕም የከተማዋ ደህንነት ለማረጋገጥና ጥቃትን ለመቀነስ ወንጀለኞችን ማሰር እንደሚጀምሩ ነው ያስታወቁት ።
በዋሽንግተን ዲሲ የቤት እጦትን ለመከላከል የሚሰራው የኮሚኒቲ ሽርክና እንደገለጸው ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች በከተማዋ ጎዳናዎች እንደሚያድሩ አስታውቋል ።
በተጨማሪም 3,275 ሰዎች በዋሽንግተን የአደጋ ጊዜ መጠለያዎችን ሲጠቀሙ፣ 1,065 ሰዎች በሽግግር መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የኮሚኒቲ ሽርክናው መረጃ ያመላክታል ።