“የአሰብን ወደብ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችው ይበሰብሳል እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም” ሲሉ አንድ ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት ጄነራል ተናገሩ፡፡
ጄነራሉ የአሰብን ወደብ “በኤርትራ በኩል ያሉ ግመሎች እንኳን አያገኙትም” ሲሉ አክለዋል፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/07/2018፡- አሰብ የሚባለው ወደብ ሲሰራ ወይም ዲዛይን ሲሆን ኢትዮጵያን ብቻ እንዲያገለግል ታስቦ ነው ሲሉ የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ተናግረዋል።
ጄነራሉ አክለውም ወደቡን ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት “ይበሰብሳል እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም” ብለዋል።
ሜ/ጄነራል ተሾመ ገመቹ ይህን የተናገሩት የባህር በር እና ወደብን አስመልክቶ በአድዋ ሙዚየም ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ሲሆን ኢትዮጵያ “እንኳን በሰጥቶ መቀበል ሕግ በነፃ የባሕር በር ይገባት ነበር” ብለዋል።
ለዚህ ንግግራቸው ሞሮኮ ለጎረቤት ሀገራት በነፃ የባሕር በር መስጠቷን በምሳሌነት ያነሱት ጄነራሉ “ሞሮኮ ምዕራብ ሰሃራ አካባቢ ላሉ ሀገሮች፣ ጎረቤታቸው ላሉ ሀገሮች በነፃ የባሕር በር ሰጥታለች። ይሄን ለመድረክ ፍጆታ ሳይሆን እዚህ ሞሮኮ ኤምባሲ መጠየቅ ትችላላችሁ። ምንም ሳያስከፍሉ በነፃ። ይሄ ታሪክ ሳይሆን አሁን በሥራ ላይ ያለ ነገር ነው። የኛ ጉዳይ የምቀኝነት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እንደ ሞሮኮ ዓይነት ልብ ስለሌላቸው ካልሆነ በስቀር እንኳን በሰጥቶ መቀበል ሕግ በነፃም ይገባን ነበር ነው” በማለት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት ተጠቃሚዎቹ “አሁን ባሕር በር አይገባችሁም የሚሉት የጎረቤቶቻችን ቡድኖች እና ግለሰቦች ናቸው” ብለዋል።
ጄነራሉ በማብራሪያቸው የአሰብን ወደብ በመጥቀስ ለኤርትራ ሳይሆን ኢትዮጵያን ብቻ እንዲያገለግል ታስቦ የተሰራ ነው ብለዋል። ይህን ወደብ “በኤርትራ ያሉ ግመሎች እንኳን አያገኙትም” በማለት አስረድተዋል።
“አሰብ የሚባለው ወደብ እራሱ ሲሰራ ዲዛይን ሲሆን ኢትዮጵያን እንዲያገለግል ብቻ ታስቦ ነው። ወይም ደግሞ አፋርን ጨምሮ ወደዚህ ያለውን ሀገር ወይም ደግሞ አቅጣጫ ብቻ እንዲያገለግል ተብሎ ስለተሰራ በዚያ [በኤርትራ] በኩል ግመልም አይደርስበትም። የግመል ውኃ መጠጫ ይባላል እንጂ አሰብ ወደብ በጀርባው በኩል ግመልም አያገኘውም። ምንም ሊሆን አይችልም።” ሲሉ የመከላከያ የውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ሜ/ጀነራል ተሾመ አክለውም “[ወደቡ] እንዲሁ መበስበስ ካልሆነ በቀር ምንም ሊሆን አይችልም። ይሄ ራሱ በዓለም አቀፍ አንድ መከራከሪያችን ነው። ጀርባውን ገልብጦ ነው ያለው በዚያ[በኤርትራ] በኩል ምንም ሊሆን አይችልም። ሲሰራ ራሱ ከአፋር ጀምሮ ወደዚህ ያለ ሕዝብ እንዲጠቀም የተሠራ ነው። አሁን እኛ ባንጠቀም እንዲሁ ይበሰብሳል። ምቀኛ የምንለውም ለዚህ ነው። እንዲሁ ይበሰብሳል እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም” ሲሉ ተደምጠዋል።



