የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ በአዳዲስ ወንጀሎች በድጋሚ ለፍርድ ሊቀርቡ ነው፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/07/2018፡- የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ በ8 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው በተፈጸሙ ከ57 ሺህ በላይ ወንጀሎች ላይ ምርመራ ሊደረግባቸው እንደሆነ ተሰምተዋል፡፡
ከጥቂት ጊዜያት በፊት ከእስር የተፈቱት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ዑመር/አብዲ ኢሌ በድጋሚ ለሕግ ሊቀርቡ መሆኑ ተሰምቷል።
አብዲ ኢሌ በ2010 ዓ.ም. በክልሉ ሁከት በማስነሳት የልዩ ኃይላቸው አባላት ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ውጊያ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጋቸውንና ለበርካታ ቤተክርስቲያኖች መቃጠል ምክንያት መሆናቸውን ተከትሎ መታሰራቸው ይታወሳል።
ይሁንና ከዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ክሳቸው ተነስቶ መለቀቃቸው በወቅቱ በጄል ኦጋዴን ተጎጂዎች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቶ ነበር፤ በአሁኑ ሰዓት ያሉበት ትክክለኛ ቦታም አይታወቅም።
ይሁን እንጂ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተቋቋመው የሽግግር ፍትህ ኮሚሽን ባደረገው ማጣራት መሠረት፣ አብዲ ኢሌ በድጋሚ በቁጥጥር ስር ሊውሉ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ግለሰቡ በ8 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው በተፈጸሙ ከ57 ሺህ በላይ ወንጀሎች ላይ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ በንጹሐን ላይ የተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች፣ የጾታ ጥቃቶች፣ በ“ጄል ኦጋዴን” እስር ቤት ይፈጸሙ የነበሩ ኢ-ሰብዓዊ አያያዞች እና የሀብት ውድመት ይገኙበታል።



