አሜሪካ ከባድ የተባሉ ጥቃቶችን ኢራን ላይ መፈጸሟን አስታወቀች፡፡

ኢትዮ ሚኒተር፡ 27/04/2018፡- አሜሪካ ባለፉት 72 ሰዓታት ኢራን ውስጥ በሚገኙ 200 ገደማ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልፃለች፡፡
በዚህም የቴህራንን የድሮን እና ሚሳዔል አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማዳከሟን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ብራድ ኩፐር ተናገሩ።
የአሜሪካ ጦር በአሁኑ ሰዓት የኢራንን ሚሳዔል የማምረት አቅም ለማውደም እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና አዛዡ፤ አሜሪካ በኢራን የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች እና መሠረተ ልማት ላይ እያካሄደች ስላለው ወታደራዊ ዘመቻ መግለጫ ሰጥተዋል።
“ባለፉት 72 ሰዓታት ብቻ አሜሪካ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች ኢራን ውስጥ በጥልቀት ገብተው 200 ገደማ ዒላማዎችን አጥቅተዋል” ብለዋል
“ባለፈው አንድ ሰዓት ብቻ ቢ-2 ቦንብ ጣዮች ባሕር ላይ የሚገኙ የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ስፍራዎችን ዒላማ በማድረግ 900 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ በርካታ ቦንቦችን ጥለዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ኩፐር “የኢራን ኤሮስፔስ ዕዝንም ዒላማ አድርገናል። ይህ እርምጃ የኢራንን አሜሪካ ላይ ስጋት የመፍጠር አቅም ያዳክማል” ሲሉም አክለዋል።
“ያለፉት 24 ሰዓታት ዘመቻን ስንመለከት ከመጀመሪያው ቀን ጋር ሲነጻጸር የኢራን ባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃቶች በ90 በመቶ፤ የድሮን ጥቃቶች ደግሞ በ83 በመቶ ቀንሰዋል” ብለዋል።
ከሐሙስ ምሽት አንስቶ ካለፉት ቀናት አንጻር “ከባድ” የተባለ ጥቃት በኢራን የተለያዩ አካባቢዎች እና ዋና ከተማው ቴህራን ውስጥ እየተፈጸመ መሆኑ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የቴህራን ነዋሪም ከተማው ውስጥ ተከታታይ ፍንዳታዎች እየተሰማ መሆኑን ገልጿል።
“ቤታችን በተከታታይ በየአምስት ደቂቃው እየተንቀጠቀጠ ነበር። ትናንት ማታ ከሁሉም የከፋው ምሽት ነበር” ብሏል።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ “አስከፊ ነበር። በጣም እየደበደቡ ስለነበር ሁሉም መስኮቶች ሲንቀጠቀጡ ነበር” ስትል ሁኔታውን አስረድታለች።
በሌላ በኩል ኢራንም በቀጣናው አገራት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች። ባህሬን በሁለት የእንግዳ ማረፊያ እና መኖሪያ ሕንጻዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አስታውቃለች።
ሳዑዲ አረቢያም እና ኳታርም በተመሳሳይ ወደ አየር ክልላቸው የገቡ ሚሳዔል እና ድሮኖችን መምታታቸውን ገልጸዋል።



