ኢራን ውስጥ ከ1,000 በላይ ንጹኃን መገደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ቡድን ገለጸ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 25/06/2018፡- አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት መፈጸም ከጀመሩበት ቅዳሜ የካቲት 21 አንስቶ ባሉት ቀናት ውስጥ በኢራን ከ1,000 በላይ ንጹኃን መገደላቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጠቅሶ የዜና ወኪል ‘ሂራና’ ዘገበ።
የዜና ወኪሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ 181 ያህሉ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆነ ሕጻናት ናቸው። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ 5,402 መሆናቸውን የገለጸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ፤ ከእነዚህ ወስጥ 100 ያህሉ ሕጻናት መሆናቸውን አክሏል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ኢራን ውስጥ ቢያንስ 104 ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቡድኑ ገልጿል። እንደ ቡድኑ ዘገባ፤ እነዚህ ጥቃቶች ወታደራዊ ካምፖችን፣ የሕክምና ማዕከላትን እና የመኖሪያ አካባቢዎችን መትተዋል።
ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለመሞታቸው የደረሱ መረጃዎች እየተመረመሩ እንደሆነም ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ጥቃት በከፈቱበት ቅዳሜ ዕለት በሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት የሞቱ ሰዎችን የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ ምሥሎች ወጥተዋል።
ሚናብ በተባለው የኢራን ከተማ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ከ160 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል። ትምህርት ቤቱ ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ካምፕ አቅራቢያ እንደሚገኝ ተነግሯል።
የአሜሪካ ጦር ክስተቱን በተመለከተ ስለሚወጡ መረጃዎችን እያጣራ መሆኑን ገልጿል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ በአካባቢው ላይ ስለተካሄደ ማንኛውም ዘመቻ “እንደማያውቅ” ተናግሯል።



