ዲፕሎማሲ
ኢትዮጵያ እና አዛርባጃን በመከላከያን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሁለትዮሽ ስምምነት መፈረማቸው ተሰማ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 2-0/06/2018፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በአዛርባጃን የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባኩ ከተማ ሲደርሱ በአገሪቱ ባለስልጣናት አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን “በአዘርባጃን ባደረግኩት የመጀመሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ላደረጉልኝ ሞቅ ያለ እና የተከበረ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርቷል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአቪዬሽን ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በነፃ የንግድ ቀጣናዎች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአዘርባጃን አቻው መካከል በተደረጉ የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ በመመስረት አጋርነታችን በየጊዜው እያደገ መጥቷል ሲሉ አስረድቷል።
እነዚህ የትብብር ዘርፎች ለሁለትዮሽ ግንኙነታችን መጠናከር መሠረት የጣሉ ሲሆን፣ ዛሬ ባደረግነው ጥልቅ ውይይትም ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን ይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተስማምተናል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የነበራቸው ውይይት ገልፆታል።
በዛሬው ዕለትም በመከላከያ እና በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነዶች ፊርማ ሥነ-ሥርዓት መደረጉ ታውቋል።



