
ኢትዮ ሞኒተር፡ 2-0/06/2018፡- ፓኪስታን የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።
ፓኪስታን ዛሬ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ታሊባን ሁለቱን አገራት በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተጋጋለ የመጣ ሲሆን፣ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼባዝ ሻሪፍ አገራቸው “ማንኛውም ጠብ አጫሪነትን የመስበር ሙሉ አቅም አላት” ሲሉ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በታሊባን ላይ “ግልጽ ጦርነት” አውጀዋል። የታሊባን ወታደራዊ ቃል አቀባይ “ጥቃት ከተፈጸመብን ምላሽ እንሰጣለን፤ ነገረ ግን ግጭት በአሁኑ ሰዓት አልጀመርንም” ሲሉ አስተባብሏል።
የታሊባን ባለሥልጣናት ፓኪስታን ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸው ከ50 በላይ ወታደሮችን መግደላቸውን እንዲሁም 19 የፓኪስታን የድንበር ኬላዎችን ማውደማቸውን እና በርካታ ወታደሮችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።
ፓኪስታን በበኩሏ ታሊባን የሚቆጣጠራቸው 27 የድንበር ኬላዎችን ማውደሟን ገልጻ፣ በታሊባን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል ብላለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲረግብ ያሳሰበ ሲሆን፣ ኢራን ሁለቱም አገሮች ለማደራደር ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጿል።



