ዲፕሎማሲ

ሶማሊላንድ ከፍተኛ ዲፕሎማቷን በእስራኤል የመጀመሪያ አምባሳደሯ አድርጋ ሾመች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/06/2018፡- ሶማሊላንድ ባለፈው ታኅሣሥ የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና በሰጠቻት እስራኤል ውስጥ አምባሳደር ሆነው የሚወክሏትን ከፍተኛ ዲፕሎማት ሾመች።

የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሞሐመድ ኦማር ሃጊ ሞሐሙድ በእስራኤል ውስጥ የአገሪቱ አምባሳደር እና ቋሚ መልዕክተኛ እንዲሆኑ መሾማቸውን ባወጣው የሹመት ደብዳቤ አሳውቋል።

በአምባሳደርነት የተሾሙት ከፍተኛ ዲፕሎማቱ በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ቀደም ሲል በውጭ ጉዳይ ላይ የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ አማካሪ እንዲሁም በታይዋን ውስጥ የሶማሊላንድ ተወካይ ነበሩ።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሹመቱ በሶማሊላንድ እና በእስራኤል መካከል በተደረሰው ስምምነት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር የሶማሊላንድ ጉብኝት መሠረት የተከናወነ መሆኑን በመግለጽ እንደተቀበለው አሳውቋል።

ጨምሮም እስራኤል በቅርቡ በሶማሊላንድ አምባሳደሯን እንደምትሾም እና በሁለቱ ወገኖች መካከል በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ ግንኙነቶችን እንደምታጠናክር አሳውቋል።

ነጻ አገርነቷን አውጃ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ተነጥላ ለቆየችው ሶማሊላንድ እስራኤል የአገርነት ዕውቅናን የሰጠችው ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም. ነው።

ይህን የእስራኤል ውሳኔ ሶማሊያ “በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው” በማለት ያወገዘች ሲሆን፤ አገራት፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትም ዕውቅናውን ተቃውመው ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለጉብኝት እስራኤል እንደገቡ ተገልጿል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እስራኤል የገቡ ሲሆኑ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስት ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ውይይት ካደረጉ በኃላ በእስራኤል ፓርላማ፣ ክኔሴት ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates