ሄዝቦላህ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ከተሳተፈ እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት እንደምትፈጸም አስጠነቀቀች፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 18/06/2018፡- ሄዝቦላህ በማንኛውም መንገድ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ፤ እስራኤል አየር ማረፊያን ጨምሮ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በሊባኖስ ላይ እንደምትፈጽም ማስጠንቀቋን ሮይተርስ ዘገበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከኢራን ጋር በምታደርገው የኒውክሌር ድርድር ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ፤ ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በአውሮፓውያኑ 2024 የተካሄደውን ጨምሮ ከእስራኤል ጋር ለበርካታ ጊዜያት የተዋጋ ሲሆን አሁንም ቡድኑ በአሜሪካ እና ኢራን ጉዳይ ሊሳተፍ ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው የሊባኖስ ባለሥልጣናት ሄዝቦላህ በአገሪቱ ዜጎች ላይ “መጥፎ ሁኔታን” ሊያመጣ በሚችል መልኩ ምላሽ እንዳይሰጥ ጥያቄ እንዳቀረቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራጂ ተናግረዋል ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጄኔቫ ውስጥ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “እስራኤላውያን የሲቪል መሠረተ ልማቶችን፤ ምናልባትም ቤሩት የሚገኘውን አየር ማረፊያ ልትመታ እንደምትችል የሚያሳዩ ምልክቶች ለሊባኖስ ደርሰዋል” ብለዋል።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ማክሰኞ ዕለት በታተመ ጋዜጣ ላይ በወጣ ቃለ መጠይቃቸው ፤ ሄዝቦላህ ሊባኖስን ወደ “ሌላ ጀብዱ” እንዳያስገባት አሳስበዋል።
አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ናኢም ቃሲም በአንጻሩ ባለፈው ወር በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፤ ቡድኑ በዋሽንግተን እና ቴህራን ጉዳይ “ገለልተኛ እንዳልሆነ” ተናግረዋል።
በዚህ ጦርነት “ሊፈጸም የሚችል ጥቃት ዒላማ እንደሆነም” መግለጻቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።



