ማህበራዊ
በካርቱም ከሦስት ዓመታት በኋላ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ መጀመራቸው ተገለፀ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 17/06/2018፡- በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተዘግተው የቆዩት በካርቱም የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በዚህ ሳምንት ዳግም መከፈታቸው ተገለፅዋል።
በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ቤት ሕንፃዎችን ለመጠገን እና በከፍተኛ መጠን እየተመለሱ ያሉ ተማሪዎችን ለመቀበል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ሲል ሱዳን ትሩቡን ዘግቧል።
የካርቱም መንግስት ትምህርት ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2023 በሱዳን ሠራዊት እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በዋና ከተማዋ የሚገኙ 280 ገደማ ትምህርት ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ማስታወቁን ዘገባው አመላክቷል።
በርካታ ትምህርት ቤቶች ለተፈናቃዮች መጠለያነት እንዲያገለግሉ ተደርገው የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በታጣቂ ኃይሎች ተይዘው ቆይተዋል።
ይህም መምህራን እና ተማሪዎች ከአካባቢያቸው እንዲሰደዱ እና የከተማዋ የትምህርት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ምክንያት ሆኖ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን አሁን ነዋሪዎች ቀስ በቀስ በአንፃራዊነት ሰላም ወደ ሰፈነባቸው የከተማዋ አካባቢዎች እየተመለሱ በመሆኑ በዚህ የትምህርት ዘመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።



