አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመች ጦርነቱ የሁለቱ አገራት ብቻ እንደማይሆን ኢራን አስጠነቀቀች፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 17/06/2018፡- አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም የተለያዩ አማራጮችን እያጤነች መሆኑ እየተገለጸ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፤ ኢራን ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ ጦርነቱ በሁለቱ አገራት መካከል ብቻ እንደማይሆን አስጠነቀቀች።
በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊካሄድ በተቃረበበት ጊዜ አሜሪካ “ከውስን የመጀመሪያ ደረጃ የአየር ጥቃት አንስቶ፣ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ለቀናት የሚዘልቅ የአየር ጥቃት ዘመቻ” ለመፈጸም እያሰበች መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
ነገር ግን ኢራን በአሜሪካ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ የሚከተለው ውጤት በሁለቱ አገራት ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ አስጠንቅቃለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ውስን የሚባል ጥቃት እንደሌለ እና የትኛውም ዓይነት በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከባድ የሆነ የአጸፋ ምላሽ እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀዋል።
እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ኢራን ከአሜሪካ የሚቀርቡላትን ቅድመ ሁኔታዎችን እንድትቀበል ለማስገደድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውስን ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ መሆናቸው ተዘግቦ ነበር።
አሜሪካ የትኛውንም ዓይነት ወታደራዊ እርምጃ በኢራን ላይ ብትወስድ አደጋዎች እንዳሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገራቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
“ሁሉም አማራጮች አደጋ አላቸው። በተለይ ደግሞ የተራዘመ ጥቃት በአሜሪካ ሠራዊት እና በጦር መሳሪያ ላይ ከፍተኛ ዋጋን ከማስከተሉ በተጨማሪ ኢራን አጸፋ የምትመልስ ከሆነ በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ አጋሮችን ለመከላከል አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል” ሲሉ ባለሥልጣኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ስጋትም በከፍተኛ የአሜሪካ ወታደራዊ እና የደኅንነት ባለሥልጣናት ስብሰባዎች ላይ ተነስቶ መነጋገሪያ መሆኑ ተገልጿል።
አሜሪካ ጥቃት ትፈጽማለች የሚለውን ዛቻ ተከትሎ ኢራን ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መርከቦች፣ የጦር ሰፈሮች እና አጋሮች ላይ ከባድ የአጸፋ ጥቃት እንደምትፈጽም በተደጋጋሚ አሳውቃለች።



