ሶስት ከፍተኛ የትግራይ ወታደራዊ ጄነራሎች ወደ አዲስ አበባ መግባታቸው አነጋገሪ ሆነ፡፡
ጄነራሎቹ አፋር ክልል ወደ ሚገኘው እና ለራሱ የሰላም ሐይል ብሎ የሚጠራው የትግራይ ታጣቂ ቡድን እንደተቃላቀሉም ታውቀዋል፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 13/06/2018፡- በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ወሳኝ እና ከፍተኛ ወታደራዊ ሚና የነበራቸው፣ እንዲሁም በቅርቡ በትግራይ ክልል ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ እና የፀጥታ ውጥረት መሃል ስማቸው ጎልቶ ሲነሳ የነበሩ ሶስት ከፍተኛ የትግራይ የጦር መሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ተረጋግጧል፡፡
ወደ መዲናዋ የገቡት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ብርጋዴር ጄኔራል ጉዕሽ ገብረ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ፍቃዱ እና ኮሎኔል ንጉሰ ወልደገብርኤል/ወለጋ መሆናቸው ታውቋል።
እነዚህ አመራሮች በህወሓት የረጅም ጊዜ የትጥቅ ትግል ታሪክም ሆነ በቅርቡ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት የላቀ ተሳትፎ የነበራቸውና በሰራዊቱ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ቁልፍ ሰዎች ናቸው።
በተለይም ብርጋዴር ጄኔራል ጉዕሽ ገብረ በቅርቡ በትግራይ ውስጥ በተፈጠረው የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ከአርሚ አዛዥነታቸው ተነስቶ የነበሩ ሲሆኑ “የሰራዊቱን ውሳኔ አንቀበልም” በማለታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ወታደራዊ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ መወሰኑ ይታወሳል።
ጄኔራል ጉዕሽ “መጀመሪያ ሻዕቢያን እና በውስጣችን ሆነው ሊያጠፉን የሚፈልጉ የሻዕቢያ ተላላኪዎችን እንታገል” የሚል ጠንካራ ፀረ-ኤርትራ አቋም በይፋ በማራመዳቸው በህወሐት ጥርስ ተነክሶባቸው ነበር።
የአሁኑ የአዲስ አበባ ጉዟቸውም ከዚህ የውስጥ ቅራኔ ጋር በተያያዘ፣ ከለውጥ ፈላጊ ኃይሎች እና ከሌሎች የትግራይ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጋር አዲስ ስትራቴጂካዊ ህብረት ለመፍጠር ያለመ ሊሆን እንደሚችል ሰፊ ግምት ተሰጥቶታል።
ሰዎስቱ ጄነራሎች ቀድሞው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ከመጡት ኮነሬል ዮውሃንስ አባተ/ወዲ አባተ የተገናኙ ሲሆኑ ለራሱ የሰላም ሐይል ብሎ የሚጠራው በዓፋር ክልል ወደ ሚገኘው የትግራይ ታጣቂ ቡድን መቀላቀላቸው ታወቅዋል፡፡



