ዲፕሎማሲ

“የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ መሆን የለበትም” አሉ የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶዋን፡፡

ኢትዮ ሚኒተር፡ 11/06/2018፡- ትናንት የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ/ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶዋን አገራቸው በአፍሪካ ቀንድ “አዲስ ግጭቶች እና ሕመም መመልከት” እንደማትፈልግ እንዲሁም ቀጣናው “የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ” መሆን እንደሌለበት ተናገሩ።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት አክለውም፤ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና “ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም” አይኖረውም ብለዋል።

ኤርዶዋን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ “ዘለግ ያለ ውይይት” እንዳደረጉ የተገለፀ ሲሆን ከ11 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው መደሰታቸውን የገለጹት የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን፤ ሁለቱ አገራት እንደ ባቡር እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ ፋብሪካዎች እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ባሉ ዘርፎች ላይም ትብብር እንዳላቸው አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ “የመላው ዓለም ዐይን ወደ የአፍሪካ ቀንድ በዞረበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የቆየ የመንግሥት መዋቅር እና ተምሳሌትነት ያለው አስተዳደር ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል” ብለዋል።

ቱርክዬ በዚህ ቀጣና አዲስ ግጭት እንዲነሳ እንደማትፈልግም ኤርዶዋን በንግግራቸው አስገንዝበዋል። “ቱርክዬ፤ ቀድሞውንም ስቃይ በደረሰበት በዚህ ቀጣና ውስጥ አዲስ ግጭቶች እና አዲስ ሕመም ፈጽሞ መመልከት አትፈልግም” ብለዋል።

“የዚህ ቀጣና ችግሮች በራሳቸው በቀጣናው አገራት ሊፈቱ እንደሚገባ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ መሆን እንደሌለበት እናምናለን” ሲሉም የቱርክን አቋም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው “የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ንግግር በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች” መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር የባሕር በር ተከልክላ፣ በዓለም ላይ ካለው ልምምድ እና አካሄድ ውጪ በጠላቶቻችን ደባ ለረዥም ጊዜ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና እንድትቆይ መደረጉ ትክክል አለመሆኑን ተወያይተናል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ “በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር” እንድታገኝ “እንደ ቱርክዬ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች በዲፕሎማቲክ መስኩ ጫና በመፍጠር” እገዛ እንዲያደርጉ መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።

ዐቢይ አክለውም፤ “ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ከዚህ አንጻር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠንከር ያለ ውይይት አድርገናል” ብለዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች የአገራቱን የንግድ ግንኙነት ለማስፋፋት እንደተስማሙ ተገልጿል። በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል ያለውን ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ መጠን “ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር መሙላት እንዲችል” ማድረግ እንደሆነ ዐቢይ ተናግረዋል።

የፀረ ሽብር ትግል እና እንዲሁም የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤን (ኮፕ) በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መነጋገገራቸውንም አክለዋል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates