Uncategorized
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የኬንያ ሠራተኞች አድማ ምክንያት በረራዎች መቋረጣቸው ተገለፀ፡፡

ኢትዮ ሚኒተር፡ 11/06/2018፡- በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዋነኛ የአገሪቱ አውሮፕላን ማረፊያ ከ20 ሰዓት በላይ በረራ በማቋረጡ ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ጉዟቸው እንደተስጓጎለ ተገለጸ።
በአፍሪካ በርካታ ተጓዦችን ከሚያስተናግዱ አየር ማረፊያዎች መካከል አንዱ በሆነው ጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ሠራተኞች ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ አድማ በማድረጋቸው በረራዎች ተሰርዘዋል።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለትምህርት ሊጓዝ የነበረው እና በረራው የተሰረዘበት ጃክ ኦኮት የተባለ ተጓዥ “ከ20 ሰዓት በላይ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ቆይቻለሁ። በሰው ተጨናንቋል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የኬንያ አብራሪዎች ማኅበር “የተፈጠረው መስተጓጎል ከአብራሪዎች የሥራ እና እረፍት ጊዜ ጋር የሚጣረስ ነው” ብሏል።
የሥራ ማቆም አድማው ከበረራ ደኅንነት ጥበቃ ጋር እንዳይጣረስ እንደሚሰጋም ማኅበሩ አስታውቋል።
የኬንያ አቪየሽን ሠራተኞች ማኅበር ከሳምንት በፊት የሥራ ማቆም አድማ እንደሚኖር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።
የበረራ ሠራተኞችን ክፍያቸው እንዲሁም የሥራ ሁኔታቸው የማይሻሻል ከሆነ ሥራ የማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ ሞስ ንዲማ “ይሄ በቀላሉ የሚታይ አድማ ሳይሆን ሙሉ ኢንዱስትሪውን የሚመለከት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።



