የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ነገ ማክሰኞ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለፀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 09/06/2018፡- የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በዚህ ሳምንት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውን የቱርክ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው እንደገለጸው፣ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ዛሬ ሰኞ ወደ አቡዳቢ ያቀኑ ሲሆን፣ በዚያም ከሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውይይታቸው በቱርክ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለውን ትብብር በማስፋት እንዲሁም በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ላይ እንደሚያተኩርም ታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብዣ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የተገለፀ ሲሆን፣ በጉብኝታቸው ወቅት ድርድራቸው ተጠናቆ ዝግጁ የሆኑ በርካታ ስምምነቶች እና ሰነዶች ይፈርማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው መረጃ ያመለክታል።
ይህ የተገለፀው በጎረቤት ሱዳን ባለው ቀጣይነት ያለው ግጭት ምክንያት ቀጠናዊ ትኩረት በጨመረበት ወቅት ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የቱርክ አምባሳደር ሰዳት ኦናል፣ አንካራ ለሱዳን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት የምታደርገውን ድጋፍ በድጋሚ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
አምባሳደሩ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ኢንስቲትዩት የሱዳን ሰብአዊ ፈንድ ዝግጅት ላይ በተሳተፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ቱርክ የሱዳን መረጋጋት ለሰፊው ቀጠና “በፅኑ አስፈላጊ እንደሆነ ታምናለች” ብሏል።



