
ኢትዮ ሞኒተር፡ 06/06/2018፡- በመቐለ ከተማ ትናንት የካቲት 5/2018 ዓ.ም ከምሽቱ 3:30 ሰዓት አከባቢ የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል።
የከተማው ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ለመቐለ ኤፍ ኤም ሬደዮ በሰጠው መረጃ መሠረት፣ ምሽት 3:30 አካባቢ በዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ መቐለ ዩኒቨርስቲ ዓዲ ሓቂ ካምፓስ ዙሪያ የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል።
በፍንዳታው የሰውም ይሁን የንብረት ጉዳት እንዳልደረሰ የገለፀው ፅ/ቤቱ ” የፈነዳው ቦምብ የመቐለ ከተማን ሰላምና ጸጥታ ለማናጋትና ሕዝቡን ለማሸበር ዓላማ ባላቸው የጥፋት ኃይሎች ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ” ብሏል።
” ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ያደረሰው ምንም ዓይነት ጉዳት ባይኖርም፣ በፍንዳታው ድምፅ በርካታ ሕዝብ ተደናግጧል ” ሲልም አክሏል።
” ፍንዳታው የመቐለ ሕዝብን ለማሸበርና የየካቲት 11 በዓል በሰላም እንዳይከበር በሚፈልጉ ተላላኪዎች ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ” ያለው ፅ/ቤቱ ” ከወራት በፊትም በተመሳሳይ ቦታ መሰል የሽብር ተግባር ተፈጽሞ ነበር ” ሲል አስታውሷል።
ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የመቐለ ከተማ ፖሊስ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ ነው እንደሆነም ገልጿል።
ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበት ያሳሰበው ፅ/ቤቱ ” ስለ ፍንዳታው አፈጻጸም እና ስለ ፈጻሚዎቹ የሚመለከት ዝርዝር ማጣራት ተጠናቆ ሲያልቅ ይፋ ይደረጋል ” ሲል አሳውቋል።



