ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የምታጋራው ድንበር ከ15 ዓመታት በኋላ ዳግም ሊከፈት መሆኑ ተሰማ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 06/06/2018፡- ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የምትጋራው ድንበር በአልሸባብ ጥቃት ምክንያት ከተዘጋ ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ በሚያዝያ ወር ሊከፈት መሆኑን የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ማስታወቃቸዉን ቢ.ቢ.ሲ ይግቧል፡፡
መቀመጫውን በሶማሊያ ያደረገው አሸባሪ ቡድኑ በኬንያ ውስጥ በርካታ ከባድ ጉዳትን ያስከተሉ ጥቃቶችን ፈጽሟል፡፡
እ.አ.አ በ2013 በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ላይ የፈጸመው ጥቃት 67 ሰዎችን ሲገድል፤ ከሁለት ዓመት በኋላ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ላይ የፈጸመው ጥቃት ደግሞ 148 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
ድንበር የመክፈቱ ዕቅድ ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2023 ይፋ የተደረገ ቢሆንም በተከታይ የተፈፀሙ ጥቃቶች ድንበር የመክፈት ዝግጅቱን አራዝመውታል።
ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እንደገለጹት ሁለቱ ሀገራት የሚጋሩትን ድንበር ለመክፈት የታሰበው ከዓመታት የጸጥታ ምዘና በኋላ ሲሆን እርምጃው የደኅንነት ስጋትን እንዳያስከትል ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል እንደሚሰማራም አክለዋል።
ኬንያ፣ በድንበሯ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች መኖራቸውንና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎችም ስለሚዘዋወሩም ሀገሪቷ ስጋት ላይ ነበረች።
የኬንያው ፕሬዝደንት ድንበር የመክፈት እቅዱን ያስታወቁት በኬንያ በሰሜን ምሥራቅ ወደምትገኘው፤ ብዛት ያላቸው ሶማሊያውያን መኖሪያ በሆነችዉ የድንበር ከተማዋ ማንዴራ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ነው፡፡
ሩቶ በኤክስ ገፃቸው “በማንዴራ ያሉ ኬንያውያን ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸው በሶማሊያ ካሉት ጋር መገናኘት አለመቻላቸው ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
የድንበሩ መከፈት “ድንበር ተሻጋሪ ንግድን እንደሚያበረታታና ለአገራችን ሕዝቦች የጋራ ብልጽግና እንደሚያሰፍን” ሩቶ ተስፋ ማድረጋቸው ተገልጿል።



