ዚምባብዌ የፕሬዚዳንቷን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የሚያስችል አዲስ ረቂቅ ሕግ አወጣች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/06/2018፡-የዚምባብዌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ83 ዓመቱ ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ቢያንስ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚፈቅድ አዲስ ረቂቅ ሕግ አፀደቀ።
አዲሱ ረቂቅ ሕግ ፕሬዚደንቶች በምርጫ ሳይሆን በምክር ቤት አባላት እንዲመረጡ እና ሰባት ዓመታት ላሉት ሁለት የሥልጣን ዘመን እንዲያገለግሉ ይፈቅዳል።
አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆነ ባለው ሕግ አንድ የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመታትን የያዘ ነው። የፍትሕ ሚኒስትሩ ዚያምቢ ዚያምቢ ረቂቅ ሕጉ ለምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ከሕዝብ ጋር ውይይት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
ሆኖም ሁለቱም ምክር ቤቶች በገዥው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ በበላይነት የተያዙ ናቸው። ቢሆንም ሕጋዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ይችላል።
የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች የሥልጣን ዘመን የሚቀየር ከሆነ ሕዝበ ውሳኔ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን አዲሱ ረቂቅ ሕግ አሁን ያሉትን ፕሬዚደንት የሚጠቅም አይደለም ሲሉም ተከራክረዋል። ምናንጋግዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን ላይ የወጡት ለረጅም ጊዜ የአገሪቷ ፕሬዚደንት የነበሩት ሟቹ ሮበርት ሙጋቤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተነሱ በኋላ እአአ በ2017 ነበር።
ከዚያም በቀጣይ ዓመት በነበረው ምርጫ ያሸነፉ ሲሆን እአአ በ2023 በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ ደግሞ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠዋል።
በአሁን ጊዜ አንድ እግራቸው ጉድጓድ ውስጥ እስከሚገባ ስልጣን ላይ ሙጡኝ የሚሉ የአፍሪካ መሪዎች እየተበራከቱ መጥቷል።



