48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 04/06/2018፡- 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ በተለያዩ ዘርፎች ባለፈው ዓመት እድገቶች እና ተግዳሮቶች እንዳጋጠሟት አስታውሰው፤ የአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ ቁልፍ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ መቻላቸውን አንስተዋል።
የዓለም ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ስጋት እየጨመረ መምጣቱን በማንሳት በተለይም አፍሪካ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድናት እና በንግድ መስመሮች ላይ የፉክክር መስክ እየሆነች መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አብራርተዋል።
የአህጉሪቱን ጥቅም ለመጠበቅ የአፍሪካ አንድነት እውነተኛ እና ጠንካራ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ፤ አፍሪካ በበጎ አድራጎት ላይ ሳይሆን በእኩልነት እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ እውነተኛ አጋርነት ያስፈልጋታል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፤ የህብረቱ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች ባከናወኗቸው ተግባራት የአህጉሩን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል።
በአብነትም የአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (አውዳ-ኔፓድ) እና የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) የሰሩትን ስራ እና ያመጡትን ውጤት ጠቅሰዋል።
የተጀመሩ ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠል የፋይናንስ ምንጭን ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበው፤ አህጉራዊ የግል ተቋማትን ከመንግሥታት ጋር ማስተሳሰር ይገባል ብለዋል።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ የስራ አስፈፃሚው ምክር ቤት ስብሰባውን ተከትሎ ይካሄዳል፡፡



