ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በቀጠናዊ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ታወቀ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 03/06/2018፡- የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጉብኝት አድርገው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሐሙድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ መሪዎች አቡዳቢ ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ውጥረት እንዲሁም በፍልስጤም እና በእስራኤል ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ተነግሯል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ መሪዎቹ ቀጠናዊ መረጋጋት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን “የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት” ማክበር ላይ የሚመሠረት ነው በማለት በአካባቢው ያለው ውጥረት የሚባባስ ከሆነ ሁሉም አገራት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲል አሳስቧል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት ባለፉት ቀናት ከቱርክ እና ከሶማሊያ አቻዎቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ያቀኑት።
ኤምሬትስ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተጽእኖ ያላት አገር መሆነዋ ይታወቃል፡፡
ሲሲ ከኤምሬትስ መሪ ጋር የምጣኔ ሀብታቸውን ትስስር ለማጠናከር ከመወያየታቸው በተጨማሪ የአገሪቱን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርስቲን በጋራ መጎብኘታቸው ተዘግቧል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ በሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻ ላይ ግዙፍ ግንባታዎችን ለማካሄድ ከግብፅ ጋር ከአንድ ዓመት በፊት ከስምምነት መድረሷ ይታወሳል።



