የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአሜሪካ የቀረበውን የሱዳን የሰላም ዕቅድ እንደምትደግፍ አስታወቀች ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/06/2018፡- የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአሜሪካ የቀረበውን እና በሱዳን ለዓመታት የተካሄደውን አውዳሚ ጦርነት ለማስቆም ያለመውን የሰላም ዕቅድ መቀበሏን አስታወቀች።
ኤምሬትስ ድጋፏን የገለጸችው፣ በሱዳን ግጭት ውስጥ ተፋላሚ የሆኑ ወገኖችን በመርዳትና ጦርነቱን በማቀጣጠል ረገድ ክስ እየቀረበባት ባለበት ወቅት ነው።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኤክስ ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ፤ አቡ ዳቢ በአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ይፋ ያደረጉትን “ሁለንተናዊ የሱዳን የሰላም ዕቅድ” በደስታ እንደምትቀበል ገልጸዋል።
ኤምሬትስ በአስቸኳይ ተኩስ ለማቆም የሚደረጉ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን የገለጸች ሲሆን፣ አሜሪካ፣ ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያን ካቀፈውና በሱዳን ጉዳይ ሽምግልና እያደረገ ካለው “ኳድ” ከተሰኘው ቡድን ጋር በቅንጅት እንደምትሠራም አረጋግጣለች።
ባለፈው ማክሰኞ በዋሽንግተን በተካሄደው የሱዳን ለጋሾች ጉባኤ ላይ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቡሎስ፣ የቀረበው የሰላም ተነሳሽነት በአምስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
የተነሱት ነጥቦችም፤ የተኩስ አቁም ማድረግ፣ ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማስቻል፣ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንዲሁም የፖለቲካ ሽግግር ማካሄድ እና የአገሪቱን መልሶ ግንባታ ማከናወን የሚሉ መሆናቸውን ዘ አረብ ኒውስ አስነብቧል።



