ዲፕሎማሲ

ሶማሊያ እና ሳውዲ አረቢያ ወታራዊ ትብብር ተፈራረሙ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/06/2018፡- ሶማሊያ እና ሳውዲ አረቢያ በቀይ ባሕር ቀጠና ላይ ያለውን የጸጥታ ትብብር ለማስፋፋት እና መረጋጋትን ለማስፈን የሚያስችል የመከላከያ እና ወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመግባቢያ ሰነዱ በሪያድ የተፈረመው በሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር አህመድ ሙዓሊም ፊቂ እና በሳውዲ አቻቸው ልዑል ካሊድ ቢን ሰልማን መካከል ነው።

ምንም እንኳን የስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች በይፋ ባይገለጹም፣ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉ የጋራ ወታደራዊ እና የመከላከያ ፍላጎቶችን የሚያካትት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፣ ይህ ስምምነት በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየጨመረ በመጣው የጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር እና የባሕር ላይ ደህንነት ስጋት ሳቢያ የተደረገ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አካል ነው።

ሶማሊያ የአየር ክልሏን ለመጠበቅ እና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር ከወዳጅ ሀገራት የምታገኘውን የቴክኒክ ድጋፍ፣ ስልጠና እና የወታደራዊ ቁሳቁስ አቅርቦት ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የሪያድ ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል።
ይህ የወታደራዊ ስምምነት የተፈረመው በሞቃዲሾ እና በሪያድ መካከል ያለው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመጣበት ወቅት ነው።

 

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates