ዲፕሎማሲ

የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት በቅርቡ ከእስራኤል ጋር የንግድ ስምምነት እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/05/2018፡- ከሮይተርስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሒ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር በቅርቡ “የንግድ ስምምነት” እንደምትፈፅም ተናግረዋል።

ሀገራቸው “በማዕድን፣ ነዳጅ እና ግብርና ሀብት የበለፀገች” እንደሆነች የተናገሩት ፕሬዝደንቱ፤ እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳልተፈፀመ ቢናገሩም በቅርቡ እንደሚፈፀም “መቶ በመቶ” እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ለቴል-አቪቭ የማዕድን መብት ለመስጠት ቃል የገቡት ፕሬዝደንት በምትኩ ሶማሊላንድ ከእስራኤል የምትፈልገው ቴክኖሎጂያዊ ትብብር እንደሆነም አስረድተዋል።

ሶማሊላንድ ለባትሪ እና ለኤሌክትሪክ መኪና ወሳኝ የሚባለውን ሊቲየም የተባለ ማዕድን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊ ሀብቶች እንዳሏት ትገልፃለች።

በአውሮፓውያኑ 2024 ኪሎማስ የተሰኘው የሳዑዲ ማዕድን አውጭ ኩባንያ ሊቲየም እና ሌሎች አስፈላጊ ማዕድኖችን ለማውጣት ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል።

አብዱላሒ ለተሰጣቸው የሀገርነት እውቅና አመስግነው ሶማሊላንድ ከእስራኤል ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ እንደምትሻ ቢገልፁም እስራኤል ወታደራዊ ሰፈር በምትገነባበት ጉዳይ ላይ ውይይት እንዳልተካሄደ አሳውቀዋል።

እስራኤልን ለመጎብኘት ከኔታኒያሁ ግብዣ ቀርቦላቸው ቢቀበሉም ቀን እንዳልተቆረጠ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን እውቅና ተከትሎ ሶማሊያ፣ ቻይና፣ ቱርክ፣ ግብፅ እና የአፍሪካ ኅብረት ቁጣቸውን አሰምተዋል።

ፕሬዝደንቱ ከእስራኤል በተጨማሪ ሌሎች የተባበሩት መንግሥት ሀገራት በተለይ ደግሞ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች እና ዩናይትድ ስቴትስ ለሶማሊላንድ እውቅና እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates