አውሮፓ
ስደተኞችን የጫነ ጀልባ ከግሪክ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከብ ጋር ተጋጭቶ 15 ሰዎች መሞታቸው ተገፀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/05/2018፡- ስደተኞችን ጭኖ ከቱርክ የተነሳ ፈጣን ጀልባ በቺዮስ ደሴት አካባቢ ከግሪክ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከብ ጋር ተጋጭቶ ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
የግሪክ ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት ግጭቱ የፈጠረው በቭሮንታደስ መንደር አቅራቢያ በሚገኘው የቺዮስ የባሕር ወሽመጥ ላይ ነው።
አደጋው በደረሰበት ወቅት ስደተኞችን የጫነው ጀልባ አደገኛ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደነበረ ገልጸዋል። የባሕር ጠባቂዎችም ክትትል እያደረጉበት እንደነበር አክለዋል።
የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች፤ ከቱርክ የባሕር ዳርቻ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደምትገኘው ቺዮስ ደሴት ስደተኞችን የምታጓጉዝ አነስተኛ ጀልባ ተመልክተው ወደ መጣችበት እንድትመለስ ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበር አንድ ባለሥልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለሥልጣኑ “አዘዋዋሪዎቹ ጀልባዋን ወደ ባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከቧ በማስጠጋት ግጭቱ እንዲከሰት አድርገዋል” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ሮይተርስ ገልጸዋል። ጀልባው ላይ ከ30 እስከ 35 የሚደርሱ ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር የዐይን እማኞች መናገራቸውን ባለሥልጣኑ አክለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች ዜግነት እስካሁን አልታወቀም።



