“ከኤርትራ ጋር ያለው ቅራኔ የጀመረው ከቀይ ባሕር ጥያቄ በፊት ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ። ጠቡ በትግራይ የመጀመሪያ ዙር ጦርነት እንደምጀምር ተናግሯል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 26/05/2018፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ጥር 26 ቀን 2018 ዓ/ም በፓርላማ ተገኝቶ ለህዝብ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ ካነሱዋቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አንዱ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ስላለው ወቅታዊ ግንኙነት የተመለከተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ችግር መነሻ የቀይ ባሕር ጥያቄ ሳይሆን፣ ኤርትራ ሀገር ሆና ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ነው የገለፁት።
ብዙዎች ከኤርትራ መንግስት ያለው ቅራኔ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኃላ እንደተከሰተ ይመስላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነታው ግን ከዛ በፊት የተከሰተ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
በለውጡ ማግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የዓመታት ችግር እንዲፈታ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፣ ሂደቱ በተፈለገው ልክ እንዳልተሳካ በመጠቆም በተለይም በትግራይ ጦርነት ወቅት የታዩ ክስተቶች ለቅራኔው መፋፋም ምክንያት መሆናቸውን አብራርተዋል::
በትግራይ የመጀመሪያ ዙር ጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ሰራዊት የለቀቃቸው ቦታዎች የኤርትራ ሰራዊት ከኃላ እየተከተለ ይገባ እንደነበረ በመግለፅ በዚህም ሽረ ገብቶ ንብረት ሲዘርፍ ጠብ ተፈጥሯል፣ እንዲሁም በአክሱም ወጣቶች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ጠቡ ተፋፍሟል ብሏል።

በዓድዋ ፋብሪካዎች ሲዘርፍ ጠቡ እንደተጋጋለ የገለፁት ጠቅላዩ ዓዲግራት ገብቶ የመድኃኒት ፋብሪካ ሲነቅልና የቀረውን ሲያወድም ጠቡ ጫፍ ደርሷል በዚህ ወቅት የትግራይ ሃብትን ማውደም ካላቆማችሁ ወያኔን መውጋት ትተን አፈ ሙዛችን ወደ እናንተ እናዙሩዋለን ብለናቸዋል ሲሉ ተደምጧል።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ አቅጣጫዎች ተወጥሮ መዋጋት የማይችልበት ወቅት ስለነበረ ይህንን ግፍ ሳይናገር ዝም እንዳለ የጠቆሙት ሲሆኑ ችግሩን በውይይት ለመፍታት የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የቀደሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በርካታ ሐላፊዎች ወደ አስመራ እስከ መላክ የተደረገው ጥረት ፍሬ አለማፍራቱን ጠቁመዋል።
ወደ መቐለ ይደረግ የነበረው ጉዞ የዘገየውም የኤርትራን ሠራዊት ከጀርባ ለመግታት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልዩነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የትግራይ ሕዝብ እፎይታ ያገኘበት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።



