
ኢትዮ ሞኒተር፡ 25/05/2018፡- የሱዳን ጦር እሁድ ዕለት ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ የደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ካዱግሊ ላይ የጣለውን ጥብቅ እገዳ ለመስበር እየተቃረበ መሆኑን ታውቋል።
ከተማዋ በ2023 ከተጀመረው ጦርነት የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ በፈጣን የድጋፍ ኃይሎች እና በአብደልአዚዝ አል-ሂሉ በሚመራው በሱዳኑ የሰሜን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ ጥምረት በከፍተኛ ሁኔታ ከበባ ውስጥ ሆና ቆይታለች።
ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ከበባ በምግብና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት እጅግ አስከፊ የሆኑ የሰብአዊ ችግሮች አስከትሏል።
ቀውሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ወደ ሰሜን ኮርዶፋን አስቸጋሪ ጉዞ ለማድረግ ሲገደዱ፣ ሌሎች ደግሞ በኑባ ተራሮች ውስጥ በሚገኙ በንቅናቄው ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች መጠጊያ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።
የወታደራዊ ምንጮች ለሱዳን ትሪቡን እንደገለጹት ጦሩ ዲሊንግ ከተማን ባለፈው ሳምንት ከተቆጣጠረ በኃላ አሁን ደግሞ ከካዱግሊን የሚያገናኘውን ስትራቴጂካዊ የአል-ዳሾል አካባቢ መቆጣጠሩን ተገልጿል።
ይህም የደቡባዊ ኮርዶፋን ከተማ ካዱግሊን ለመቆጣጠር ትልቅ እርምጃ እንደሆነ እየተገለፀ ነው።
የሱዳን ጦር ድሮኖች በመጋጠሚያ አካባቢ፣ በአልዳሾል እና በኪጋ አልቃይል በሚገኙት የታጣቂ ቡድኑ እና ሸሪኮቹ ቦታዎችን ኢላማ በማድረግ ቀጣይነት ያለው የአየር ድብደባ እያካሄደ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን እነዚህ ጥቃቶች የእግረኛ ወታደሮች ወደ ካዱግሊ እንዲገሰግሱ እና እገዳውን እንዲያቆሙ ለማድረግ የታሰቡ መሆናቸውን ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እያለ የሱዳን አየር መንገድ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ካርቱም አየር ማረፊያ በረራ ያደረገ ሲሆን ይህም ከተማይቱ ወደ ሰላማዊ መረጋጋት እየተመለሰች መሆኗ ማሳያ እንደሆነ ተጠቁሟል።



