
ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/05/2018፡- አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚለው ስጋት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጠባቂዎች የአሜሪካን እና የእስራኤልን እንቅስቃሴዎች “በጥንቃቄ እና በቅርበት እየተከታተለ” መሆኑን አስታውቋል።
ፕሬስ ቲቪ ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ የኢራን የጦር መኮንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ ዋሽንግተን በኢራን ላይ የሚወሰድ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ የተሳካ ይሆናል ብላ ማሰቧ ስለ ቴህራን ወታደራዊ አቅም ያላት ግንዛቤ “የተሟላ ስላልሆነ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ቀጠና እየተጠጉ መሆናቸውን ተከትሎ፣ የኢራን አብዮታዊ ጠባቂዎች የምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል መሀመድ ፓክፖር ባለፈው ሳምንት ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ጄኔራሉ እንዳሉት፣ የኢራን ጦር “ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ሆኖ፣ ጣቱ በቃታ ላይ ” ይገኛል ሲሉ ተደምጦ ነበር።
አክለውም አሜሪካ እና እስራኤል ዋጋ የሚያስከፍል “ማንኛውንም ዓይነት የተሳሳተ ስሌት” ከመውሰድ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የአሜሪካ ቁልፍ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በኢራን ላይ ለሚሰነዘር ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ግዛቷ መነሻ እንዲሆን እንደማትፈቅድ አስታውቃለች።
የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ኤምሬትስ የምድር፣ የአየር ወይም የውሃ ክልሏ ኢራንን ለመምታት በሚደረግ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲውል አትፈቅድም።
በተጨማሪም ለእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ምንም ዓይነት የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንደማታደርግ አቋሟን ግልጽ አድርጋለች።



