የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውስጥና የውጭ የስጋት ኃይሎችን እንቅስቃሴዎች የሚቀለብሱ ስምሪቶች ማከናወኑን አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 15/05/2018፡- የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በ2018 በጀት ዓመት አስቀምጧቸው የነበሩ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን የማጽናት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን ጨምሮ የአደባባይ ክብረ በዓላት እንዲሁም ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የማድረግ፤ የተቋማዊ የሪፎም አጀንዳዎችን የመከለስና ለሀገራዊ ምርጫው ስኬት የሚረዱ ዝግጅቶች በላቀ ደረጃ ተፈፅመዋል ብለዋል፡፡
ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በተከናወኑ ስምሪቶች በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የስጋት ኃይሎችን በማዳከም ረገድ መሰረታዊ ለውጥ የተመዘገበ መሆኑ በመግለጫው የጠቀሰው ድርጅቱ በተሳሳተ መንገድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ከሕግ ማስከበር አማራጭ ጎን ለጎን መንግሥት በሚያቀርበው የሰላም ጥሪ አማካኝነት ትጥቅ እየፈቱ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚረዱ ስምሪቶች መከናወናቸውም በስኬትነት አንስተዋል፡፡
በሀገራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ የሚቃጡ ስጋቶችን መቀልበስ መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭ የደኅንነት ምህዳር ውስጥ የኢትዮጵያን ከፍታና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት የሚያረጋገግጡ ስትራቴጂክ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑ ገልፀዋል፡፡
በግማሽ የበጀት ዓመቱ ተቋሙ የተሰጡትን የመረጃ፣ የደኅንነትና የሥነ-ልቦና ጦርነት የተልዕኮ ሥራዎች በላቀ መንገድ የመፈጸም አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉያመለከተ ሲሆን በዚህም ስጋቶችን ከመቀልበስ ባሻገር ቀድሞ ችግሮችን በመለየትና አዝማሚያዎችን በመተንተን ድንገተኛ የሚባሉ የደኅንነትና የፀጥታ ክፍተቶችን ማስቀረት መቻሉ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
አሁንም ግን ሰላምና ፀጥታ የማጽናት ሂደቱ ያልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች የፈጠሩት ግንባር እንዲሁም ቀጣናውን የኃይል አሰላለፍ ፍጥጫ በማድረግ ረገድ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ተግዳሮቶች መሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡



