የተለያዩ
ፌደራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት ከ445 ኪሎ ግራም በላይ አደገኛ እፅን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/05/2018፡- የ13 ሀገራት ዜግነት ያላቸው 19 ግለሰቦች በዝውውሩ ሲሳተፉ መያዛቸውንም ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከ445 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ አደገኛ ዕፅዋትን ከነአዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ይህም ከ2017 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዝውውሩ መጠን መቀነሱን ጠቅሶ የቁጥጥር ሂደቱ ዘመናዊ አሠራር የተከተለ በመሆኑ ውጤታማነቱ መጨመሩን ገልጿል።
በተካሄዱ የቁጥጥር ስራዎች ኮኬይንና ካናቢስ የተባሉ አደገኛ ዕፅዋት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፀው ፀረ-ፈንጅና አደገኛ እፅዋት ዝውውር ቁጥጥር መምሪያ በተከናወኑ ጠንካራ የፍተሻና የክትትል ሥራዎች የ13 ሀገራት ዜግነት ያላቸው 19 ግለሰቦች በዝውውሩ ሲሳተፉ መያዛቸውን ገልጿል።
በአደንዛዥ ዕፅዋት ዝውውር ወንጀል በቁጥጥር ሥር ባዋላቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የገለፀው ፌደራል ፖሊስ ከዚህ ቀደም በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች ከ2 ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን አስታውሷል።
በቀጣይም አደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአዘዋዋሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለፁን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።



