አሜሪካ የሶስት አገሮች ሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን በሽብርተኝነት ፈረጀች፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 06/04/2018፡- የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን (Muslim Brotherhood) የሊባኖስ፣ የዮርዳኖስ እና የግብጽ ቅርንጫፎች ላይ የሽብርተኝነት ፍርጃ መጣሉን አስታወቁ።
የውሳኔው ዝርዝር በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የወጣውን “ኤግዚኩቲቭ ኦርደር 14362” ተከትሎ በተወሰደው በዚህ እርምጃ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሊባኖሱን የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን “የውጭ ሀገር የሽብር ድርጅት” እና “ልዩ ዓለም አቀፍ አሸባሪ” በሚል ፈርጆታል። የቡድኑ መሪ የሆኑት ሙሀመድ ፋውዚ ታኮሽ በተመሳሳይ በሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ ተካትተዋል።
በተጓዳኝ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር፤ የግብጽ እና የዮርዳኖስ የሙስሊም ወንድማማቾች ቅርንጫፎችን ለሀማስ ቁሳዊ ድጋፍ በመስጠት በሚል ክስ “ልዩ ዓለም አቀፍ አሸባሪ” ሲል ፈርጇቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በሰጡት መግለጫ፣ ይህ እርምጃ በአሜሪካ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን ቅርንጫፎችን አቅም እና እንቅስቃሴ ለማዳከም በፕሬዝዳንት ትራምፕ የተያዘው ቁርጠኝነት የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
“እነዚህ ፍርጃዎች የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን ቅርንጫፎች የሚያደርሱትን ጥቃት እና አለመረጋጋት ለመግታት የተጀመረው ቀጣይነት ያለው ጥረት መጀመሪያ ናቸው” ያሉት ሩቢዮ፤ አሜሪካ ቡድኖቹ ለሽብር ተግባር የሚውል የገንዘብ አቅም እንዳያገኙ ያሉትን አማራጮች ሁሉ እንደምትጠቀም አጽንኦት ሰጥተዋል።



