አፍሪካ

የሱዳን መንግሥት ከሦስት ዓመት ገደማ ጦርነት በኋላ ወደ ዋና ከተማዋ ካርቱም ተመለሰ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 04/04/2018፡- መቀመጫውን በፖርት ሱዳን አድርጎ የከረመው የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት፤ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ወደ ዋና ከተማዋ ካርቱም ተመለሰ።

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል ኢድሪስ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “የተስፋው መንግሥት” በይፋ ወደ ካርቱም መመለሱን ገልጸዋል።

በጦርነት ለተሰቃዩት የከተማዋ ነዋሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ጥረት እንደሚጀምርም ተናግረዋል።

በአገሪቱ ጦር የሚመራው መንግሥት ካርቱም ለቅቆ የወጣው፤ በአውሮፓውያኑ 2023 የእርስ በርስ ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በመገፋቱ ነበር።

ሠራዊቱ ባለፈው መጋቢት ላይ ከተማዋን መልሶ መቆጣጠር ችሏል። ካርቱም ለዓመታት ከቆየው ውጊያ እያገገመች ትገኛለች።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ግጭቱ በበረታበት ወቅት አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከከተማዋ ተሰድደዋል።

ከከተማዋ ለመውጣት ያልፈለጉ ወይም ያልቻሉ ነዋሪዎች ደግሞ፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተቆጣጠረበት ዘረፋ እና ታጣቂዎች የሚፈጽሙትን የንጹሃን ቤት ነጠቃ ጨምሮ እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣን ኡጎቺ ዳንኤል በጥቅምት ወር እንደገለጹት፤ መሰረታዊ አገልግሎቶች “በጭራሽ አይሰሩም” በሚያስብል ሁኔታ ላይ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢድሪስ፤ መንግሥት በካርቱም ያለውን የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን ለማሻሻል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአውሮፓውያኑ 2026 ለሱዳን “የሰላም ዓመት” እንደሚሆን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የእስር በርስ ጦርነቱ ከፈነዳ በኋላ በሀገሪቱ ቢያንስ 150,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የተባበሩት መንግስታት በሱዳን ያለውን ሁኔታ፤ በዓለም ላይ አስከፊው ሰብአዊ ቀውስ ሲል ይገልጸዋል። ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችም ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates