መካከለኛ ምስራቅ
የየመኑ የደቡብ ሽግግር ምክር ቤት መሪ ወደ አቡዳቢ መኮብለላቸው ተሰማ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 01/05/2018፡- መሪው በሶማሊላንድ በኩል ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መኮብለላቸው የገለፀው በሳውዲ ዓረብ የሚደገፈው የየመን ጥምረት ነው።
በየመን የሚንቀሳቀሰው ተገንጣይ ቡድን የደቡብ ሽግግር ምክር ቤት (STC) መሪ አይዳሩስ አል-ዙበይዲ በሶማሊላንድ በኩል አድርገው ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መኮብለላቸውን በሳውዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር አስታውቋል።
ጥምር ጦሩ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ አል-ዙበይዲ በሪያድ ተከታታይ የሰላም ንግግሮች እንዲሳተፉ በታቀደው መሠረት ሳይገኙ ቀርተዋል።
መሪው ረቡዕ ዕለት በሌሊት ከአደን ወደ ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ በጀልባ ተሳፍረው “በውድቅት ሌሊት ማምለጣቸውን” መግለጫው ጠቁሟል።
እንደ መግለጫው ከሆነ፣ አል-ዙበይዲ በርበራ ከደረሱ በኋላ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መኮንኖች ጋር በመሆን በአውሮፕላን ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ ተጉዘዋል።
“አውሮፕላኑ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ሲበር ማንነቱን የሚገልጹ የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቶችን አጥፍቶ የቆየ ሲሆን፣ በአቡ ዳቢ ወደሚገኘው አል ሪፍ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ለመድረስ 10 ደቂቃ ሲቀረው መልሶ አብርቷል” ሲል ጥምረቱ በዝርዝር አስታውቋል።



