የአፍሪካ ህብረት የሱድን መንግስት ያቀረበውን የሰላም እቅድ መደገፉን የሱዳን ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተቃወመው፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 23/04/2018፡- የሱዳን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአገሪቱ መንግስት የቀረበውን የሰላም እቅድ መቀበሉን በመቃወም የህብረቱ እርምጃ ቀደም ሲል ከነበረው ቀጣናዊ ስምምነት የወጣ አደገኛ አቅጣጫ መሆኑንና የተቋሙን ወገንተኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል ኢድሪስ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በበጎ ተቀብለዋል። ሊቀመንበሩ ጥሪውን ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል “ጽኑ መሰረት” ሲሉ ገልጸውታል።
የሰላም እቅዱ በርካታ ነጥቦችን የያዘ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል አባላት ከተቆጣጠሯቸው ከተሞች ወጥተው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በአረብ ሊግ እና በአፍሪካ ህብረት ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አስቀድሞ ስምምነት የተደረገባቸው ካምፖች እንዲገቡ የሚል ይገኝበታል።
በተጨማሪም ጥሪው እነዚህን ኃይሎች በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ፊት ትጥቅ የማስፈታት ሂደት እንዲጀመርና የጦር መሣሪያዎች በድጋሚ እንዳይንቀሳቀሱ ዋስትና እንዲሰጥ ይጠይቃል።
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የአብዮታዊ ኃይሎች ሲቪል ዲሞክራሲያዊ ጥምረት (ሶሙድ)፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ማህሙድ አሊ ዩሱፍን ተችቷል።
ጥምረቱ የኮሚሽነሩ ድጋፍ የአፍሪካ ህብረት አመራሮች በፖርት ሱዳን ለሚገኘውና በሠራዊቱ ለሚመራው መንግስት የሚያሳዩት “የተለመደ ወገንተኝነት” አካል ነው ሲል ከሷል።



