የተባበሩት መንግስታትን እና አሜሪካ የ2026 የሰብአዊ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 21/04/2018፡- ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን በ2026 በተባበሩት መንግስታት በኩል የአሜሪካን እርዳታ ለመቀበል ከተዘጋጁ 17 ሀገራት መካከል እንደሆኑ ተገለፀ።
በተባበሩት መንግስታት እና አሜሪካ መካከል የተፈረመውን የ2 ቢሊዮን ዶላር የሰብአዊ ድጋፍ ስምምነት ተጠቃሚ ከሚሆኑ 17 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ድጋፉ በ2026 በተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ፕሮግራሞች በኩል እንደሚተላለፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሰኞ ዕለት በጄኔቫ በይፋ የተፈፀመው ይህ ስምምነት የተባበሩት መንግስታት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የሰብአዊ እርዳታ ስራዎችን ለመደገፍ አሜሪካ ቃል ገብታለች።
የተባበሩት መንግስታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ቶም ፍሌቸር ስምምነቱን በግጭት ምክንያት በተፈጠረው መፈናቀል፣ በምግብ ዋስትና ማጣት እና በአየር ንብረት መናወጥ ምክንያት የሰብአዊ ፍላጎቶች አጣዳፊ ለሆነባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ለማዳን የሚረዳ ታሪካዊ ቁርጠኝነት እንደሆነ አድንቀዋል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፍሌቸር ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሰሩ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን አመስግነው፣ እያለቀ ያለውን አመት “በሰብአዊነት ተግባር ላይ ለተሰማሩ ሁሉ በጣም አስቸጋሪ ዓመት” ሲሉ ገልጸውታል።
“በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በጣም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ያገኛሉ” ሲሉ ድጋፉ በሚቀጥለው ዓመት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን እንደሚረዳ አክለዋል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ዩክሬን፣ ሄይቲ፣ ናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ምያንማር፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ)፣ ባንግላዲሽ፣ ሶሪያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ቻድ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ እና ኤል ሳልቫዶር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቀዋል፡፡
ገንዘቡ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ 87 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ ያለመውን የተባበሩት መንግስታት የ2026 የሰብአዊ ዕቅድ ለመደገፍ የታሰበ ነው ተብለዋል።



