አውሮፓ
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የ90 ቢሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማማ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 16/04/2018፡- የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ለዩክሬን ቢያንስ ለሁለት ዓመታት የሚሆን 90 ቢሊዮን ዩሮ የጋራ ብድር ፋይናንስ ለማድረግ ወስነዋል።
የሩስያ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ ውሳነ ላይ ግን መሪዎቹ አልተስማሙም ተብሏል።
ኪየቭ በ2026 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የገንዘብ እጥረት ሊያጋጥማት ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት በዚህ ወቅት በብራስልስ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተደረሰው የእኩለ ሌሊት ስምምነት ለኪየቭ እጅግ በጣም ወሳኝ ተብሏል።
“የዛሬው ውሳኔ ዩክሬን እራሷን ለመከላከል እና የዩክሬንን ህዝብ ለመደገፍ አስፈላጊውን መንገድ ይሰጣታል” ሲሉ የአውሮፓ ምክር ቤት ኃላፊ አንቶኒዮ ኮስታ ተናግረዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በኤክስ ላይ እንደጻፉት ስምምነቱ “ጽናታችንን በእውነት የሚያጠናክር ጉልህ ድጋፍ ነው” ሲሉ አወድሷል።
“የሩሲያ ንብረቶች እንቅስቃሴ አልባ ሆነው እንዲቀጥሉ እና ዩክሬን ለሚመጡት ዓመታት የፋይናንስ ዋስትና ማግኘቷ አስፈላጊ ነው።” ሲሉም ዘለንስኪ አክሏል።
የክሬምሊን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተደራዳሪ ኪሪል ዲሚትሪቭ በቴሌግራም ላይ በጻፉት ጽሑፍ “የሩሲያን ንብረቶች ለዩክሬን ፋይናንስ በሕገ-ወጥ መንገድ አለመጠቀማቸውን” በደስታ ተቀብለዋል፣ “ለጊዜው ሕግ እና የጋራ አስተሳሰብ ድል አግኝተዋል” ብለዋል።



