የመን 180 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገወጥ መንገድ በሻብዋ የባህር ዳርቻ መድረሳቸውን አስታወቀች።

ኢትዮ ሞኒተር፡13/04/2018፡- የመን የሚገቡ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት 180 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ በሚገኘው የሻብዋ የባህር ዳርቻ መድረሳቸውን የየመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ትናንት እሁድ ባወጣው መግለጫ፣ የሻብዋ አካባቢ የደረሱት 180 ስደተኞች በአራት ሶማሊያውያን በሚመራ የኮንትሮባንድ ጀልባ ከአፍሪካ ቀንድ የተነሱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መሆናቸውን ገልጿል።
መግለጫው እንዳስታወቀው፣ የሻብዋ አካባቢ የፀጥታ ባለስልጣናት የስደተኞችን ፍልሰት ለመግታት እና ህገ-ወጥ ሰርጎ ገብነትን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰዱ ነው።
ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት ያወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው በህዳር ወር ብቻ 17,659 ስደተኞች ወደ የመን ገብተዋል።
በጥቅምት ወር ደግሞ የገቡት ስደተኞች ቁጥር 17,685 ነበር ብሏል።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተፈናቃዮች መከታተያ መረጃ ከሆነ፥ ጅቡቲ በ67 በመቶ ቀዳሚዋ የስደተኞች መነሻ አገር ሆና ቀጥላለች።
ሶማሊያ 31 በመቶ እንዲሁም ኦማን 2 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዘዋል።
ምንም እንኳን የመን የፀጥታ ሁኔታዋ እና በአገሪቱ ያለው የሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ ቢመጣም፣ ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመሻገር ለሚሞክሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች እንደ ዋና መሸጋገሪያ መስመር ሆና ማገልገሏን ቀጥላለች።
ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ በኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎች እጅ ለከፋ መከራ እና ብዝበዛ እንደሚጋለጡ ዥንዋ ዘግቧል።



