ኬንያ በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ 18 ዜጎቿን ወደሀገራቸው መመለሷን ገለጸች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 10/04/2018፡- ኬንያ በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ 18 ዜጎቿን ወደሀገራቸው መመለሷንና መውጫ ያጡ ሌሎች ተጨማሪ ኬንያውያን ዜጎች አሁንም በሩስያ ጦር ካምፕ ውስጥ የሚገኙ መሆነቸውን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከዚህ ቀደም ሁለት መቶ ኬንያውያን ለሩስያ ለመዋጋት ቅጥረኛ ኃይሎችን መቀላቀላቸውን የኬንያ ባለስልጣናት ገልጸው የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ወደሀገራቸው የተመለሱት በሩስያ-ዩክሬን ጦርነት ሲሳተፉ የነበሩ 18ቱ ኬንያውያን ዜጎች ከሁለት መቶዎቹ መካከል መሆናቸውን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ተናግረዋል።
ከጦርነቱ የተመለሱት ዜጎች ወደማገገሚያ ማዕከል እንዲገቡና ወደመደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በሩስያ የተለያዩ የጦር ካምፖች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ወደሀገራቸው እንዲመልሳቸው የኬንያን መንግስት እየተማጸኑ ያሉ ቀሪ ኬንያውያን ዜጎች መኖራቸውን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
በቅጥረኛ ወታደር መልማዮች ተመልምለው የሩስያን ጦር ከተቀላቀሉትና ለመቀላቀል ሞክረው ሳይሳካላቸው ከቀሩ ኬንያውን ዜጎች መካከል የተጎዱ መኖራቸውንም በሞስኮ የኬንያ ኤምባሲ አረጋግጧል።
የዩክሬን መንግስት በበኩሉ ከመላው አፍሪካ 1 ሺ 400 የሚሆኑ አፍሪካውያን፤ አንዳንዶቹ ተታልለው በቅጥረኝነት ከሩስያ በኩል ተሰልፈው በዩክሬን ውጊያ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ባለፈው ወር ገልጾ እንደነበር ቲ.አር.ቲ አፍሪካ ዘግቧል።



