በቀይ ባህር እና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና “ድምጽ አልባ” ነገር ግን አደገኛ የሆነ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሽግግር እየተካሄደ መሆኑን አፍሪካ ሪስክ ኮንትሮል የተሰኘ ተቋም አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 10/04/2018፡- የዓለም ትኩረት በምስራቅ አውሮፓ እና በመካከለኛው ምስራቅ ግጭቶች ላይ ባረፈበት በዚህ ወቅት፣ በቀይ ባህር እና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና “ድምጽ አልባ” ነገር ግን አደገኛ የሆነ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሽግግር እየተካሄደ መሆኑን አፍሪካ ሪስክ ኮንትሮል የተሰኘ ተቋም ባወጣው አዲስ የስትራቴጂክ መረጃ ትንታኔ አስታወቀ።
ተቋሙ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፤ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ውጥረት፣ እንዲሁም እየጨመረ የመጣው የአሜሪካ፣ የሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ የግብፅ፣ የኢራን፣ የሩሲያ እና የቻይና ጣልቃ ገብነት ከአሁን በኋላ እንደ ተናጠል ክስተቶች የሚታዩ አይደሉም።
እነዚህ ጉዳዮች በአለም አቀፍ የንግድ መስመሮች፣ በወደብ ተደራሽነት እና በስትራቴጂካዊ ጥምረት ዙሪያ ወደሚያጠነጥን “አንድ ወጥ የሽኩቻ ስርዓት” እየተዋሃዱ መምጣታቸውን ትንታኔው አመላክቷል።
የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ይህንን አደገኛ ሽግግር እንደሚያሳዩ ሪፖርቱ ጠቅሷል። የሳውዲ አረቢያ መንግስት ለዋሽንግተን ባቀረበው ጥሪ፣ የሱዳን ጦርነት እንደ ሩቅ የአፍሪካ ቀውስ ሳይሆን “የቀይ ባህር ደህንነት ስጋት” ተደርጎ እንዲወሰድና አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ መጠየቁ የለውጡ አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ በፖርት ሱዳን ያደረጉት ከፍተኛ ጉብኝት፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አሰላለፍን ያሳየ ነው ሲል ጥናቱ ገልጿል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ተደራሽነት እና በቀጠናዊ ተጽዕኖ ዙሪያ ካለባት ፍላጎት ጋር ተያይዞ ውስጣዊና ውጫዊ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እያረፉባት መሆኑ ተጠቅሷል።
የቀይ ባህር መስመር ከፍተኛ ድርሻ ያለው የዓለም የኮንቴይነር ንግድ የሚተላለፍበት በመሆኑ፣ በሱዳን የሚፈጠር ግጭት ወይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሚፈጠር ስህተት የሚያስከትለው መዘዝ ከአፍሪካ ቀንድ የዘለለ እንደሆነ የARC ትንታኔ አመልክቷል።



