ፖለቲካ
ጄኔራል አልብሩሀን በሪያድ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ጋር በድብቅ መወያየታቸው ተገለፀ፡፡
ውይይቱ በሰብአዊ እርዳታ ላይ የተመሰረተ እንደነበር ታውቀዋል፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 08/04/2018፡- የሱዳን ወታደራዊ መሪ የሆኑት ሌተና ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልብሩሀን ሳኡዲ አረቢያ መሄዳቸውን ትላንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚያም አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንን ጨምሮ ከሳኡዲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው መገለፃቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁንና ይህንን ውይይት አድርገው ከወጡ በኋላ አንድ ያልጠበቁት እንግዳ እንዳጋጠማቸው የጠቀሰው የሱዳን ትሪቢዩን ዘገባ በሪያድ የጠበቋቸው የፕሬዝደንት ትራምፕ የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቦሉስ ነበሩ ይላል፡፡
አልብሩሀን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ ‹‹ማሳድ ቦሉስ የሱዳንን ቀውስ እያባባሰ ነው፡፡ እጁን ከሱዳን ላይ ያንሳ›› የሚል ጠንከር ያለ መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ትላንት በሪያድ ከማሳድ ቦሉስ ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር መገደዳቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን በዋቢነት የጠቀሰው ዘገባው አልብሩሀን ከማሳድ ቦሉስ ጋር ያደረጉት ውይይት ከፍተኛ የሰብአዊነት ቀውስ ባለባቸው ዳርፉርና ኮርዶፋን ግዛቶች እርዳታ በሚደርስበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጿል፡፡
እነዚህ ሁለት ግዛቶች አሁን በተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ቁጥጥር ስር ቢሆኑም አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ሰብአዊ እርዳታ ማስገባት መጀመራቸው ይታወቃል፡፡



