የማይናማር መንግስት ኢትዮጵያን ጨምሮ አገራት ዜጎቻቸውን እንዲረከቡት ጥሪ አቀረበ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/04/2018፡- የማይናማር ወታደራዊ መንግስት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በእስር ቤቶች የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎችን አገሮቻቸው እንዲረከቧቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በድረገፅ በሚደረግ ማማለያ ተታለው ወደማይናማር የሚሄዱ የተለያየ አገር ዜጎች እንዳሉ ከዚህ ቀደም በስፋት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ከእነዚህ መካከል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሚገኙበት ሲሆን ወጣቶቹ ማይናማር ከገቡ በኋላ በእስር ላይ ሆነው የቀን ስራ እንደሚሰሩ በስፋት ሲገለፅ ቆይቷል፡፡
የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ከእነዚህ እስር ቤቶች አምልጠው ወደአገራቸው መመለሳቸውም አይዘነጋም፡፡
የማይናማር ወታደራዊ መንግስት በቅርቡ በእነዚህ እስር ቤቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ያደረገ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በሺ የሚቆጠሩ የተለያዩ አገር ዜጎችን አስለቅቆ አሁን በማቆያ ጣቢያ አስቀምጧቸዋል፡፡
የማይናማር አገር ውስጥ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ጄኔራል ኡንግ ካይው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እነዚህን የውጭ አገር ዜጎች መቀለብ እየከበዳቸው መምጣቱን ገልፀው አገሮቻቸው እንዲረከቧቸው ጠይቀዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሚሆኑት ቻይናዊያን መሆናቸውን ገልፀውም ከ100 እስከ 300 የሚሆኑ ዜጎች ያሏቸው ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ቬተናም፣ ኬንያና ህንድ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሺ የሚቆጠሩት የውጭ ዜጎቹ ከታይላንድ ድንበር አጠገብ በሚገኝ ማቆያ ስፍራ ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት ሚኒስትሩ የተጠቀሱትን አገራት ‹‹ዜጎቻችሁን ውሰዱልን›› ሲሉ መናገራቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡



