ኢኮኖሚ
አይ ኤም ኤፍ እና ኢትዮጵያ በባለሙያዎች ደረጃ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለፀ።
ይህም ኢትዮጵያ 261 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 203/04/2018፡- ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የአራት ዓመት የተራዘመ የብድር አቅርቦት ፕሮግራም አራተኛው ዙር ውይይት ማድረጉን ተከትሎ በባለሙያዎች ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል።
ስምምነቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አመራርና የቦርድ አስፈጻሚ አካል የመጨረሻውን ይሁንታ ካገኘ በኋላ ወደ 261 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለኢትዮጵያ እንዲለቀቅ ያስችላል ተብሏል።
አይ.ኤም.ኤፍ ይህን ያስታወቀው ታኅሣሥ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው።
ስምምነቱ የተደረሰው ከጥቅምት 20 እስከ ህዳር 4/2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ የተካሄዱትን ውይይቶች ተከትሎ ሲሆን፣ ከህዳር 24- 26/2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በበይነ-መረብና በአካል በተደረጉ ተጨማሪ ስብሰባዎች መጠናቀቁ ተገልጿል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እንዳስታወቀው፣ ስምምነቱ ቀደም ሲል በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም የጸደቀው እና 3.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበለት የተራዘመ የብድር አቅርቦት ፕሮግራም አካል ነው።
ቀጣዩ ዙር ብድር ሲለቀቅ፣ ተቋሙ ከአጠቃላይ ብድሩ ውስጥ እስካሁን ለአገሪቱ የለቀቀው የገንዘብ መጠን 2.134 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል።



