60 ሺሕ የማይሞሉ ጥቂት የዓለማችን ከበርቴዎች ግማሹ የምድራችን ሕዝብ መያዝ ከሚገባው ሦስት እጥፍ የበለጠ ሃብት መያዛቸውን ሪፖርት ይፋ አደረገ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 203/04/2018፡- ሦስት አራተኛው የዓለማችን ግለሰባዊ ሃብት አሥር በመቶ በሚሆኑ ሃብታሞች እጅ መሆኑም ተመላክቷል።
በቁጥር 60 ሺሕ የማይሞሉ ጥቂት የዓለማችን ከበርቴዎች ግማሹ የምድራችን ሕዝብ መያዝ ከሚገባው ሦስት እጥፍ የበለጠ ሃብት መያዛቸውን የዓለም ኢ-ፍትሐዊነት 2026 ሪፖርት ይፋ አደረገ።
አሥር በመቶ የሚሆኑት እጅግ የናጠጡ ሃብታሞች ሦስት አራተኛ፤ በሌላ አባባል 75 በመቶ የሚሆነውን ሁሉንም ዓይነት የዓለማችን ግለሰባዊ ሃብቶች ጠቅልለው መያዛቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።
በዓመቱ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ባለበት እየረገጠ መሆኑን የጠቆመው የተቋሙ ዓመታዊ ሪፖርት ሃብት ብቻ ሳይሆን ኃይልና ስልጣንም በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በሚገኙት የላይኞቹ ከበርቴዎች እጅ ብቻ ተከማችቶ የሚገኝ መሆኑንም አመልክቷል።
ሊጠናቀቅ 19 ቀናት ብቻ በቀሩት የአውሮፓውያኑ 2025 አሥር በመቶ የሚሆኑት እጅግ የናጠጡ ጥቂት የዓለማችን ሃብታሞች 75 በመቶ የሚሆነውን ሁሉንም ዓይነት የዓለማችን ግለሰባዊ ሃብቶች ጠቅልለው መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ 40 በመቶ የሚሆኑት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃብታሞች የዓለምን 23 በመቶ ሃብት፤ ከመካከለኛ በታች የሚገኘውና ሃምሳ በመቶ የሚሆነው ግማሹ የዓለማችን ሕዝብ ደግሞ ከዓለም አጠቃላይ ሃብት ሁለት በመቶዋን ብቻ ይዟል ተብሏል።
ከ1990ዎቹ ጀምሮ የቢሊየነሮችና ጠቅላላ ሃብታቸው ከመቶ ሚሊዮን ዶላርና ከዚያ በላይ የተመዘገ ባለመቶ ሚሊዮን ዶላር ሚሊየነሮች ሃበት በያመቱ የስምንት በመቶ ዕድገት የሚያስመዘግብ መሆኑን ያመላከተው ሪፖርቱ፤ ይህም ከመካከለኛ በታች የሆነው ግማሹ የዓለማችን ሕዝብ በዓመት ከሚያስመዘግበው የሃብት ዕድገት በእጥፍ የላቀ መሆኑን አስገንዝቧል።
በአሁኑ ሰዓት 0 ነጥብ 001 በመቶ ብቻ የሚሆኑትና በቁጥር ከ60 ሺሕ የሚያንሱት ባለብዙ ሚሊዮን ዶላር ሚሊየነሮችና ጥቂት የዓለማችን ከበርቴዎች ብቻ ግማሹ የምድራችን ሕዝብ መያዝ ከሚገባው ሦስት እጥፍ የበለጠ ሃብት በቁጥጥራቸው ስር መያዛቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ይህም የዓለማችን ሃብት የሃብት ማማ ላይ የሚገኙት እጅግ በጣም ጥቂት ከበርቴዎች እጅ በፍጥነት እየተከማቸ በመምጣቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠረው የዓለም ሕዝብ ዛሬም የዕለት ሆዱን ለመሸፈን የሚታገልባትና ጥቂቶቹ ደግሞ ከልክ በላይ በሆነ መንገድ የዓለምን የገንዘብ ኃይል ጠቅልለው የተቆጣጠሩባት እጅግ ኢ-ፍትሐዊ ዓለም እንድትፈጠር ማድረጉን አመላክቷል።



