ኢኮኖሚ
ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ካሉ 40 አገሮች ጋር የሚያስተሳስር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።
ፕርጀክቱ እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/04/2018፡- ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 40 የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የባቡር ትራንስፖርት ትስስር የሚያሳድግ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከናይጄሪያ ኢንሳይት ዳይናሚክስ ሪሶርስስ ጋር ‹‹ጋዝን በባቡር›› የኢኮኖሚ ኮሪደር (Gas-by-Rail Economic Corridor) ንቅናቄ ማስጀመሪያ የመግባቢያ ስምምነት፣ ሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በይፋ ሲፈረም ነው የተገለጸው።
ፕሮጀክቱ ከሳሃራ በታች የሚገኙ 40 አገሮችን ከ73 ሺ ኪ.ሜ በላይ በሚሸፍን የባቡር መሰረተ ልማት የሚያገናኝ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ከ500 ቢሊዮን እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በመጪው ዓመት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ስብሰባ ለውይይት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።



