የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ የሚሰጥበትና ውጤት ይፋ የሚሆንባቸው ቀናቶች አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/03/2018- ቦርዱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ባደረገው የጸደቀ ያለው ድምፅ የሚሰጥበት ቀን ግንቦት 24 ፤ የምርጫ ውጤት ደግሞ ሰኔ 4 ይፋ እንደሚደረግ ገልጿል።
በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት በመጪው ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ምዝገባው የሚከናወነው ከጥር 1 እስከ የካቲት 1 ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይሆናል ያለው ቦርዱ የምርጫ ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ጊዜ ከጥር 1 ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 እንደሚቆይም በጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል።
እንደ ዕጩዎች ምዝገባ ሁሉ አንድ ወር ጊዜ የተሰጠው የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 እንደሆነ ምርጫ ቦርድ አመልክቷል።
በቴክኖሎጂ በመታገዝ ራሳቸውን ለሚመዘግቡ (self registration) መራጮች በአንጻሩ 2 ወር የተጠጋ ጊዜ ተመድቦላቸዋል።
በዚህ ሂደት የሚሳተፉ መራጮች የሚመዘገቡት ከጥር 15 እስከ መጋቢት 7 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
መራጮች ሰኞ ግንቦት 24 ድምጻቸው ከሰጡ በኋላ ውጤቱን በምርጫ ጣቢያ ደረጃ በማግስቱ መመልከት እንደሚችሉ በጊዜ ሰሌዳው ላይ የተመላከተ ሲሆን በምርጫ ክልል ደረጃ ጊዜያዊ ውጤት የሚገለጸው፤ ከድምጽ መስጪያው ማግስት ጀምሮ እስከ ግንቦት 29 ድረስ ባሉት 5 ተከታታይ ቀናት እንደሆነ ተቀምጧል።
የምርጫ ክልሎች ውጤቶችን ለምርጫ ቦርድ የሚያስረክቡት ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 1 ድረስ ባሉት ጊዜያት እንደሚሆንም በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ውጤቶችን የማረጋገጥ ስራዎችን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2 ባሉት ቀናት ካከናወነ በኋላ ይፋዊ የምርጫ ውጤቱን ሐሙስ ሰኔ 4 እንደሚገለፅ አስታውቋል።



