አፍሪካ

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 26/03/2018፡- የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ በዋሺንግተን ዲሲ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ያስቆማል የተባለ የሰላም ስምምነት እና ሰፊ ቀጠናዊ የምጣኔ ኃብት ውህደት ማዕቀፍ ተፈራርሟል።

በተጨማሪም አሜሪካ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ “የኢኮኖሚ እና የሀብቶች ደህንነትን ለማስቀጠል እና የረጅም ጊዜ ልማትን ለሁለቱም አገራት ጥቅም ለማጎልበት የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው” ቃል በመግባት ረጅም የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተገኙበት የተፈረመውን ይህን የሰላም ስምምነት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ እና የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ አድንቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ “ለዓለም፣ ለአፍሪካ ታላቅ ቀን ነው፤ እነዚህ ሁለት አገራት ሊኮሩበት የሚገባ ብዙ ነገር አላቸው” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ካጋሜ በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕን “ለማንም የማያዳሉ” መሪ በማለት ሰላም ለማምጣት ያለውን ዕድል “ወዲያውኑ” የተጠቀሙ ናቸው ብለዋቸዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል ስምምነት ተፈርሞ ነበር፥ ነገር ግን ስምምነቱ ወዲያውኑ የፈረሰ ሲሆን ለዚህም ሁለቱ አገራት አንዳቸው ሌላኛቸውን ከስሰዋል።

ከስምምነቱ በፊት በማዕድን ሀብት በበለፀገው የምሥራቅ ኮንጎ በመንግሥት እና በሩዋንዳ ይደገፋል በሚባለው አማፂ መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር።

ትራምፕ አገራቸው ከሁለቱም አገራት ጋር ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ለመጠቀም የሚያስችል “አዳዲስ የዕድል በሮችን የሚከፍት” የተባለ ስምምነት መፈራረሟን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ ለአስርት ዓመታት በቀጠናው ሲካሄድ የቆየው ጦርነት እንዲቆም እና ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረስ፣ አማፂያን ትጥቃቸውን እንዲፈቱ፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንዲመለሱ እንዲሁም አዲስ የኢኮኖሚ ብልጽግና ማዕቀፍን የያዘ መሆኑን ትራምፕ በሰላም ሰምምነቱ ወቅት ተናግረዋል።

ትራምፕ “በሁለቱ መሪዎች ላይ ጠንካራ እምነት አለኝ” ያሉ ሲሆን “ይህንን የገባነውን ቃል እንጠብቃለን” ብለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates