ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ሰውረዋል የተባሉ 24 የስፖርት አወራራጆች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለፀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/03/2018፡- ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ሰውራዋል የተባሉ በርካታ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ተቋሙ እንዳለው ግለሰቦቹ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል ተጠርጥረው ነወ የተያዙት።
በተወሰደው እርምጃ በደኅንነት አገለግሎቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የ24 የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው መሆናቸው ተገለጿል።
የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ሥርዓቶችን ከሚያካሂዱላቸው የአገር ውስጥ የክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር የገንዘብ ስወራውን ፈጽመዋል ተብሏል።
ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር የሚባሉት የአገር ውስጥ የገንዘብ ክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ተቋማቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ይታወቃል።
እነዚህ ድርጅቶች የደንበኛን ምሥጢር መጠበቅ የሚል ሙያዊ አሠራርን “እንደ ሽፋን ተጠቅመው” የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ደብቀዋል ወይንም አሳንሰው አቅርበዋል ተብሏል።
የብሔራዊ መረጃ እና የደኅንነት አገልግሎት በዚህ የተነሳ የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች “በግብር ስወራ እንዲሁም ከፍተኛ የአገር ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው” አመልክቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በጋራ መሥራታቸውም ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት የፌደራል ፖሊስ በማዳበሪያ ግዢ ሙስና ፈፅሟል ተብሎ የተጠረጠሩት 11 ባለስልጣንናትም በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።



